ፖሊስ የዳውድ ኢብሳ መኖሪያ ቤትን ከቦ በማደር ዛሬ ጠዋት ዐራት የኦነግ አመራሮችና...

ፖሊስ የዳውድ ኢብሳ መኖሪያ ቤትን ከቦ በማደር ዛሬ ጠዋት ዐራት የኦነግ አመራሮችና አባላትን በቁጥጥር ሥር አዋለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ትናንት ከኦነግ ሊቀመንበርነታቸው በታገዱት ዳውድ ኢብሳ መኖሪያ ቤት ለተመረጡ ሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ከነበሩ ግለሰቦች መሀል ዛሬ ጠዋት ሦስቱ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

ከትናንት ጀምሮ ቤታቸው በፀጥታ ኃይሎች የተከበበው ኦነግን ከዐሥራ አምስት ዓመት በላይ የመሩትና በሰላማዊ ትግል ስም የትጥቅ ትግል ከሚያደርገው ቡድን ጋር ግንኙነት እያደረጉ ናቸው በሚል የሚወነጀሉት ዳውድ ኢብሳ አሁንም ከመኖሪያ ቤታቸው አለመውጣታቸውን ታማኝ ምንጮቻችን አረጋግጠውልናል።
የፀጥታ ኃይሎች ትናንት የተወሰኑ የኦነግ አመራሮች ሲሰጡት የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰዐቱ ደርሰው እንዲቋረጥ ካስገደዱ በኋላ፣ መግለጫውን በማሰራጨት ላይ የነበሩ 6 ጋዜጠኞችን እና የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎችን እንዳሠሩ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር የግንባሩን ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ባቴ ኡርጌሳን ጠቅሶ ዛሬ ዘግቧል።
በኦነግ ሥራ አስፈጻሚ ከግንባሩ አመራርነት የታገዱት እነዚህ አመራሮች መግለጫ እየሰጡ የነበሩት ከወራት በፊት ከግንባሩ ሊቀመንበርነታቸው ታግደዋል በተባሉት ጃል ዳውድ ኢብሳ መኖሪያ ቤት ውስጥ ነበር።
በቅርቡ ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለም፣ ሥልጣን ላይ ያለውን አካል አንቀበልም በማለት የተናገሩት የዳውድ ኢብሳን መኖሪያ ቤት ፖሊስ ጋዜጣዊ መግለጫውን ካቋረጠ በኋላ ከቦ ያደረ ሲሆን፣ ሦስት የግንባሩን አመራሮችን ጨምሮ ዐራት ግለሰቦች ዛሬ ከግቢው በመኪና ሲወጡ በፖሊስ ተይዘው መወሰዳቸው ታውቋል።
ከተያዙት አመራሮች መሀል ዳውድ ኢብሳ ባይኖሩበትም አሁንም በእርሳቸው ቤት አካባቢ የጸጥታ ኃይሎች ማንዣበባቸውን ተከትሎ በቀጣይ ቀናት ግለሰቡ ሊያዙ ይችላሉ ተብሎ ተገምቷል።

LEAVE A REPLY