ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጥራት የጎደላቸው ምርቶችን ማስታወቂያ አስተላልፈዋል የተባሉ አራት ብዙኃን መገናኛ 23 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ቅጣት ተላለፈባቸው።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን 4 መገናኛ ብዙኃን ላይ የገንዘብ ቅጣቱ መተላለፉን በብሮድካስት ባለሥልጣን የህግና ማስታወቂያ ተወካይ ዳይሬክተር ዮናስ ተስፋዬ አረጋግጠዋል፡፡
ቅጣቱ የተላለፈባቸው ጥራቱን ያልጠበቀ ምርት ማስታወቂያ በመልቀቃቸው ሲሆን፣ ኃላፊነታቸውን ተወጥተው ባለመገኘታቸው በሚል በማስታወቂያ አዋጁ መሰረት ከ10 እስከ 23 ሚሊየን ብር እንዲቀጡ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ማስታወቂያውን በግድየለሽነት በመሥራት ለመገናኛ ብዙኃኑ ሰጥተዋል የተባሉት የማስታወቂያ ድርጅቶችም ላይ ቅጣት እንደተፈጸመባቸው ታውቋል።
ቅጣቱ ስለመተላለፉ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ቅጣቱ የተላለፈባቸውን መገናኛ ብዙኃንን ዝርዝር ከመናገር ግን ተቆጥበዋል።
የብሮድካሰት ባለስልጣን የንግድ ወድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመሆን በማስታወቂያዎች በኩል ወደ ህብረተሰቡ የተሳሳተ መረጃ እንዳይሰራጭ ቁጥጥር በማድረግ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።
የተቀመጠውንም መመሪያ ተላልፎ የተገኘ የመገናኛ ብዙሀን አስመጪ ድርጅቶችም ይሁን የማስታወቂያ ድርጅቶች ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ እስከ ፍቃድ መሰረዝ አይነት እርምጃዎች ይወሰዳሉ ሲሉ አቶ ዮናስ ነግረውናል፡፡
የማስታወቂያ አዋጅ በሀገራችን ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነ ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡