ጋዜጠኛ ተመስገን በፍትህ መፅሄት ላይ ከውስጥ አዋቂ አገኘሁት የሚለው መረጃ “ወ/ሮ አዳነች አበቤ በአካውንታቸው ውስጥ 40 ሚሊየን መገኘቱን በመጥቀስ በፓርቲ ግምገማ ሲደረግባቸው እሳቸውም ማን ይህን ያህል ብር በአካውንታቸው እንዳስገባ እንደማያውቁ ሆኖም የሆነ የማያውቁት ግለሰብ ይህን ብር በአካውንታቸው ማስገባቱን አምነዋል” የሚል ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ መፅሄቱ ይህን መረጃ ሲያወጣ፣
እንዲህ አይነት መረጃ እንዲሁ በውስጠ አዋቂ በፓርቲ ግምገማ ተነሳባቸው በሚል ሳይሆን አካውንታቸው ውስጥ ይህን ያህል ብር መገኘቱን የሚያውቅ ሆኖም መረጃውን ማውጣቱ ቢታወቅ ስጋት የሚያድርበት ሰው ከሆነ እና ይህንም መረጃ ለእነፍትህ መፅሄት ያሳያቸው ቢሆን የበለጠ ታማኝነት ይኖረዋል።
የውስጠ አዋቂውን አምነው ካወጡ ደግሞ የተሳሳተ መረጃ መሆኑን በሌላ ተቃራኒ መረጃ ከተሞገቱ ያወጡት መረጃው ስህተት መሆኑን አምነው ይቅርታ መጠየቅ፣
አልያም መረጃው ልክ ነው በማለት በህግ ለመሟገት መዘጋጀት ነው። መረጃው የሰጣቸው ሰው ማንነት የማሳወቅ ግዴታ የለባቸውም። ለሀገር ደህንነት ሲባል ካልሆነ መረጃ የሚያቃብልን ሰው ማንነት ይፋ ማውጣት አይገደድም።
ፖሊስስ ተመስገንን የሚያስርበት አግባብ ከየት የመጣ ነው?
በርካታ አስተዳደራዊ እርከኖችን እና የመፍትሄ መንገዶችን በመዝለል “ህግ ጥሰሃል” በሚል ያለፍርድቤት መጥሪያ ጋዜጠኛን ማሰር እንዴት ያለ ህግ የማስከበር መንገድ ነው?
እነ አዳነች አበቤ ማድረግ የሚችሉት ለፍትህ ጋዜጣ መረጃው ሀሰት መሆኑን፣ እንዲህ አይነት ግምገማ አለመደረጉን፣ የተባለውን ማስተባበያ እሳቸው አለመስጠታቸውን፣ ውስጥ አዋቂ የተባለውን ሰው መረጃ በአግባቡ ታማኝነቱ በማጣራት የተሳሳተ መረጃ የተሰጣቸው መሆኑን ደርሰውበት የእርማት ፅሁፍ እንዲያወጡ (ይቅርታ እንዲጠይቁ) ደብዳቤ መፃፍ ነው። ለደብዳቤውም በፅሁፍ ምላሽ እንዲሰጣቸው መጠየቅ ነው።
በዚህ መንገድ አጥጋቢ ምላሽ ካላገኙና ፍትህ መፅሄት በአገኘሁት መረጃ እርግጠኝነት እፀናለሁ ካለ ወደ ብርድካስት ባለስልጣን የመመሪያ ጥሰትን በመጥቀስ ክስ ማሰማት ነው።
በፍርድ ቤትም መክሰስ ያዋጣኛል ባይ ሊሞክረው ይችላል። ሆኖም ይህ የማያዋጣ ነው።
ለምን ቢሉ
ባለስልጣን ወደ ህዝብ አገልግሎት ሲመጣ ስሜ ጠፋ ከሚለው የግል ክብሩ ይልቅ ሚዲያው ያሚያወጣው መረጃ ለህዝብ ጥቅሙ ከፍተኛ ስለሆነ፣ ማንኛውም ሰው ወደ ስልጣን ሲመጣ በተለያዩ አሉባልታዎች ስሙ ሊጠፋ እንደሚችል አውቆ የሚገባበት ስለሆነ፣ “የስም ማጥፋት” ክስ ለባለስልጣን የማይስማማ እና ፍርድቤትን የማያሳምን ክስ ነው።
የስም ማጥፋት ለባለስልጣን “ሀሰት መሆኑን እያወቀ፣ ሆነብሎ ጉዳት በባለስልጣኑ ላይ ለማድረስ” የሚል አገላለፅ በህጉ ውስጥ መኖሩ ክሱን ለማስረዳት ያከብደዋል። ገዜጠኛ ደግሞየህዝብ አይንና ጆሮ ስለሆነ ከተሳሳተ በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ የእርማት ማስተካካያ ማውጣት እንጂ ወደ ክስ የሚሄድ አይደለም።
ያዋጠኛል ባይ ይህን ክስ ሲያቀርብ ወንጀል ነው ብሎ ያመነ ፖሊስ የእስር ማዘዣ ከፍርድቤት ወጥቶ ነው አንድ ጋዜጠኛ በህግ ቁጥጥር ስር የሚውለው። ጋዜጠኛን ከማሰር ለፖሊስ ቃሉን እንዲሰጥ ቢደወልለት ሊመጣ ይችላል። የተቋም ጉዳይ ስለሆነ፣ ወንጀል ሰራ ቢባል እንኳ በዋስ ሊከላከል ይችላልና።
ሌላው
የከንቲባው ፅህፈትቤት ለብሮድካስት ያስገባው ደብዳቤ በከንቲባው ሴክረተሪ ነው።
ከንቲባችን ተነካች አይነት ክስ ነው። ወደ ፍርድቤት የሄደ ክስ የለም።
እዚህ መቀላቀል የሌለበት የባለስልጣን ጉዳይን እና የመንግስት ጉደይን ነው። ባለስልጣን ሊተች፣ ሊነቀፍ እና እንዲህ ያለ “ገንዘብ በአካውንቱ ተገኘ” ሊባል ይችላል። መረጃው ልክም ሆነ ስህተት ጉዳዩ የመንግስት ሳይሆን የባለስልጣን ግለሰቡ ነው። እዚህ ጋ ባለስልጣንን ከ መንግስትነት መለየት ግድ ይላል።
ተመስገንን ያለ ፍርድቤት ትዕዛዝ ማሰር እጅግ አደገኛ እርምጃ ነው። በርካታ ህጋዊ መንገዶችን የዘለለ ከማናለብኝነት የመነጨ እብሪተኝነት ነው። ብልፅግና እየሄደ ያለበት መንገድን ሊያስተውለው ይገባል።