ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የምስራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ በአቶ ልደቱ ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ ህግ እየተጣሰ እንደሚገኝና ጉዳዮ ከአቅሙ በላይ እንደሆነ አስታወቀ።
ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት ሁለት ጉዳዮችን ለማየት ነበር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። የመጀመሪያው የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ሁለት ግዜ የተላለፈውን የአቶ ልደቱን በዋስ መብት ልቀቁ ትእዛዝ ባለማክበሩ በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በኩል ትእዛዙ እንዲደርሳቸው፣ እንዲሁም አቶ ልደቱን የማይለቁም ከሆነ ምክንያታቸውን ቀርበው እንዲያስረዱ ነበር።
በሁለተኛ ደረጃ ልደቱ አያሌው በተጠረጠሩበት ህገ ወጥ መሣሪያ የዐቃቢ ህግ ምስክሮችን ለማድመጥ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ጉዳይ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንም ሆነ ከቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በችሎት ተገኝቶ አቶ ልደቱ እስካሁን ከእስር ያልተፈቱበትን ምክንያት ያስረዳ የለም።
” ይሄ ችሎት ለከሳሽም ሆነ ለተከሳሽ እኩል መብት ነው የሚሰጠው፤ በዚህ ረገድ ፍርድ ቤቱ በፖሊስ ላይ እያሳየ ያለው ትግስት ተገቢ አይደለም” በማለት ቅሬታቸውን የገለጹት አቶ ልደቱ አያሌው፤ ” ከዚህ ችሎት ፍትህ አገኛለሁ ብዬ እንዴት አስባለሁ? አሁን ለፖሊስ ያሳየውን ትእግስት በተራው ዜጋ ላይ ወይንም በእኔ ላይ ያደርገዋል ወይ?” ሲሉም ችሎቱን ጠይቀዋል።
ሁኔታው ከአቅም በላይ እንደሆነባቸውና አሁንም አቶ ልደቱ በዋስ ይውጡ የሚለው ውሳኔያቸውን እንደሚያከብሩ ያስረዱት ዳኞችም፤ ” እኛ ያለን አቅም ውሳኔያችን ተፈፃሚ እንዲሆን ማዘዝ ነው፤ ይህንን ትእዛዝ የሚያስፈፅም ጦር ሠራዊት የለንም፣ ጦር ሠራዊት ቢኖረን አዘን እናስፈታህ ነበር። ፖሊስ እየጣሰ ያለው ህገ መንግሥቱን ነው፣ ተቋሙን እየናቀ ያለው የእኛን ተቋም ሳይሆን የራሱን ተቋም ነው” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ አዳነ ታደሰ ገልጸዋል።
ችሎቱ በስተመጨረሻ የቢሾፍቱ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ሓላፊ እና ወንጀል መከላከል ቢሮ ሓላፊው ለምን በተደጋጋሚ ከፍርድ ቤት የሚሰጥን ትእዛዝ እንደማያከብሩ ቀርበው እንዲያስረዱ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ደግሞ አቶ ልደቱን በአስቸኳይ እንዲፈታ ውሳኔ አስተላልፏል።
ከፍርድ ቤት የተላለፈውን ትእዛዝም አቶ ልደቱን አጅቦ የሚመጣው ሳጅን መሀመድ አሊ የሚባለው የፖሊስ ባልደረባ እንዲያደርስ ሲታዘዝ፤ ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የተላለፈውን ትእዛዝ ደግሞ በአቶ ልደቱ ጠበቃ በኩል እንዲደርስ ተወስኗል።