የአማራ ክልል እየተስፋፋ የመጣው የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለው የከፋ ጉዳት አሳስቦኛል አለ

የአማራ ክልል እየተስፋፋ የመጣው የአንበጣ መንጋ እያደረሰ ያለው የከፋ ጉዳት አሳስቦኛል አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣው የአንበጣ መንጋ በምሥራቃዊ የአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የሥርጭት አድማሱን እያሳደገና የጉዳት መጠኑም እየከፋ መምጣቱንየክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በአማራ አራት ዞኖች (ሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ) በሚገኙ 20 ወረዳዎች ላይ መንጋው በከፍተኛ ሁኔታ መከሰቱን ይፋ ያደረገው የአማራ ክልል፤ የበረሃ አንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር በቀን 80 ሺህ ሄክታር መሬት ርጭት ማካሄድ ቢያስፈልግም እስካሁን ከ20 ሺኅ ሄክታር እንደማይበልጥም ጠቁሟል።
በምሥራቃዊ የአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የተከሰተው የበርሃ አንበጣ መንጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሥርጭት ዓድማሱ እየሰፋና የጉዳት መጠኑም እየከፋ መጥቷል፡፡ እስካሁንም በክልሉ አራት ዞኖች ላይ መንጋው ሰብል እያወደመ ይገኛል ነው የተባለው።
በ218 ሺኅ ሄክታር መሬት ላይ የተከሰተው የበርሃ አንበጣ መንጋ በ70 ሺኅ ሄክታር መሬት ላይ በሚገኝ ሰብል ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ መሆኑን ያስታወሰው የክልሉ ግብርና ቢሮ፤ መንጋውበሰብል ላይ ብቻ ሳይሆን በእንስሳት መኖ ላይም የከፋ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ይታወቅልኝ ብሏል።
ጉዳቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ተዘዋውረው ምልከታ ያደረጉት የግብርና ሚስትር ዴኤታው አቶ ወንዳለ ሀብታሙ መንግሥትና ሕብረተሰቡ ጉዳቱ የከፋ እንዳይሆን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረው ሥርጭቱን ለመግታት ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል ሲሉም ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ አስረድተዋል።
የጉዳት መጠኑ ከቦታ ቦታ ቢለያይም በሁሉም አካባቢዎች ያለው አደጋ በእጅጉ አሳሳቢ እንደሆነበት ነው የአማራ ክልል መንግሥት ያስታወቀው።
የበርሃ አንበጣ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው የመከላከል ሥራ በሦስት መንገዶች እየተከናወነ መሆኑን የሚናገሩት የአማራ ክልል ግብርና ምክትል ቢሮ ሓላፊ ፋንታሁን መንግሥቴ ስርጭቱን ለመግታት ባህላዊ ዘዴዎች፣ በተሽከርካሪና በሰው ኃይል የኬሚካል ርጭት እና የሄሊኮፕተር ኬሚካል ርጭት ተግባር እየተከናወኑ ይገኛል ሲሉም ተደምጠዋል።
በምስራቅ አማራ በሰብል ከተሸፈነው 998 ሺኅ 517 ሄክታር መሬት ውስጥ 4.5 በመቶ ያህሉ በአንበጣ መጎዳቱን ተከትሎጉዳት ለደረሰባቸው አርሶአደሮች የዕለት ምግብ ድጋፍ ማጓጓዝ እንደተጀመረም ክልሉ ይፋ አድርጓል።

LEAVE A REPLY