ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ የ 28 ሺኅ አባወራዎች ሰብል ሙሉ በሙሉ መውደሙን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።
በሀብሩ ወረዳ ቀበሌ 027 አካባቢ ለምቶ የነበረው ጤፍ እና ማሽላ ሙሉ በሙሉ ፍሬዉ መበላቱን ለአዲስ ማለዳ ያረጋገጠው የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት፤ በሀብሩ ወረዳ 39 ቀበሌዎች እንዳሉና 17 ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ 9 ሺኅ 100 ሄክታር ሰብል፣ 60 ሺኅ ሄክታር ግጦሽ፣ 53 ሺኅ ሄክታር ደን እና 60 ሺኅ ቁጥቋጦ መውደሙን አስታውቋል።
የወረዳው ግብርና ጽሕፈትቤት ሓላፊ ተመቼ ሲሳይ
እንደገለጹት፤ አንበጣዉ ሙሉ በሙሉ ውድመት ባደረሰባቸው 17 ወረዳዎች፣ 141 ሺኅ 240 ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚስፈልጋቸው ተናግረዋል።
የቀበሌ 027 አርሶ አደር የሆነው ወጣት ሀሰን ኑርዬ ሦስት ሄክታር ጤፍ አልምቶ ሁሉም እንደወደመበት ለአዲስ ማለዳ የገለፀ ሲሆን፣ በስፍራው የተገኘው ሪፖርተርም እንደተባለው ሰብሉ ሙሉ በሙሉ መውደሙን መመልከት ችሏል።
“ሳንሰደድ እና ልጆቻችን በረሃብ ሳይጎዱ መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ሊደግፈን ይገባል” ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ አካባቢው የበረሃ አንበጣ ከሚፈለፈልበት አፋር ክልል አጎራባች በመሆኑ፣ ከባለፈው 2012 ዓ.ም የመኸር ወቅት ጀምሮ የችግሩ ሰለባ እንደሆኑም ገልፀዋል።