ኢትዮጵያ ነገ ዜና || መንግሥት ባለፉት ሦስት ወራት ካከናወናቸው ስኬታማ ሥራዎች መካከል የብር ኖት ለውጡ አንዱ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
በ31 ቻርተር አውሮፕላን አዲሱ የገንዘብ ኖት ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሥራ ሂደቱም በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በሚስጥር ተጠብቆ መቆየቱን ለምክር ቤት አባላት አስረድተዋል።
አዲሱ የገንዘብ ኖት በ6 ሺኅ 628 የባንክ ቅርንጫፎች ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ መሰራጨቱን እና 1.3 ሚሊዮን ሰዎች አዲስ የባንክ አካውንቶች መከፈታቸውን የገለጹት የብልፅግና መሪ፤ በእነዚህ የባንክ አካውንቶች ውስጥም 37 ቢሊዮን ብር መቆጠቡንና በእስካሁኑ ሂደትም የጎላ ችግር አለመከሰቱን አስረድተዋል።
ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የመቀየሪያ ጊዜ ማብቃቱንና አነስተኛ መጠን ያለውን የብር ኖት የመቀየር ሥራ ግን እንደሚቀጥል የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እጅግ የተሳካ ሥራ መሠራቱንና ይህ እንዲሆን ባንኮች፣ የመንግሥት የጸጥታ አካላት፣ ብሔራዊ ባንክ እና የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቡድን ከፍተኛ አስተዋፅ በማድረጋቸው ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የባንኮች ቁጥር እየጨመረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባንኮች መጨመር ቁጠባን ከፍ እንደሚያደርግ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ምንም እንኳን የባንኮች ቁጥር ከፍ ይበል እንጂ ዲጂታል ባንኪንግ የሚፈለገውን ያክል ለውጥ እንዳልመጣ ከመግለጻቸው ባሻገር፣ የባንኮች የካፒታል አቅም ከፍ እንዲል እና ግዙፍ ባንኮች እንዲፈጠሩ በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።