ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁሉም ባንኮች የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ እና አስተዳደርን በተመለከተ የሚመሩበትን የተሻሻለ መመሪያ አሰናድቶ ሥራ ላይ እንዲያውሉት ማድረጉን አስታወቀ።
ብሔራዊ ባንክ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ባንኮች ለማን እና ለምን የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው የተሻሻለ መመሪያ እንደተሰናዳላቸው ይፋ አድርጓል።
የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ አሁንም ሠፊ እንደሆነ የብሔራዊ ባንክ ገዥው ይናገር ደሴ የ3 ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የገለፁ ሲሆን፣ ባንኮች የውጭ ምንዛሪን በቀዳሚነት ለመድኃኒት፣ በሁለተኛ ደረጃ ለግብርና እና ማምረቻ ዘርፍ እንዲያውሉ መመሪያ እንደተላከላቸው አስረድተዋል።
መመሪያው ባንኮች የውጭ ምንዛሪን በዘፈቀደ እንዳይሰጡ እንደሚገድባቸው የተናገሩት አቶ ይናገር ደሴ፤ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃ እና መለዋወጫ ከውጭ እንዲያስገቡበት 85 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
በዚሁ ጊዜ ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ 33 ነጥብ 46 ቢሊየን ብር ተገኝቷል ነው የተባለው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በ3 ወር የሥራ አፈፃፀሙ 200 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ከወርቅ ሽያጭ ማግኘቱን አስታውቋል።
መንግሥት በ3 ወር ውስጥ ከብሔራዊ ባንክ ለበጀት ጉድለት እንዳልተበደረ ያስረዱት የባንክ ገዢው፣ ይህን ለማካካስ ከግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጩ የተገኘ ገቢ እንደተጠቀመም ገልፀዋል።