ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ሦስት የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮቹ መታሰራቸውንና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በድርጅቱ ላይ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እያደረገበት እንደሚገኝ ገለፀ።
የግንባሩ ቃለ አቀባይ አብዱልከድር ሀሰን ኢርሞጌ አዳኒ በሶማሌ ክልል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት የቆራሄ ዞን ሊቀመንበር መሃመድ ጂግሬ ገመዲድ፣ ምክትላቸው ተማም መሃመድ ማህሙድና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና ለረዥም አመታት ፓርቲውን በሥራ አስፈፃሚነት ያገለገሉት መሃመድ ኢብራሂም ሙርሳል መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሓላፊ ኡመር ፋሩቅ ወርፋም ለቢቢሲ ሶማሊኛ በሰጡት ቃል ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በትናንትናው ዕለት፣ ጥቅምት 11/2013 ዓ.ም ልዩ ፖሊስና የቀብሪ ደሃር ፖሊስ መሃመድ ኢብራሂም ሙርሳልን በቁጥጥር ስር ያዋለቸው ሲሆን፣ ሌሎቹ አመራሮች ደግሞ ጥቅምት 10/2013 ዓ .ም በቁጥጥር ሥር እንደተያዙ ነው የተገለጸው።
“ኦብነግ ሰላሙን እያከበረ መሆኑ ክልሉን አበሳጭቷል” ሲል አቋሙን በቲውተር ላይ ያስፈረው ኦብነግ፤ ሦስቱ የፓርቲው ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ህገወጥ ነው በማለትም ድርጊቱን በይፋ ኮንኖታል።
ከ30 ዓመታት በላይ በትጥቅ ትግል ላይ የነበረው ግንባሩና የመገንጠል ፖለቲካን ያራምድ የነብረው ኦብነግ፤ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከመንግሥት ጋር የሰላም ስምምነት የተፈራረመው ከሁለት ዓመት በፊት ጥቅምት 11፣ 2010 ዓ.ም በአስመራ ከተማ መሆኑ አይዘነጋም።
በገባሁት ስምምነት መሠረት ሕጋዊና ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያካሄድኩ ነው የሚለው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) የታሠሩበትን ሦስት ከፍተኛ አመራሮችም ጉዳዮ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር በድርድር ለማስፈታት ማሰቡን ገልጿል።