ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሰብኣዊ መብት ጥሰት ስዊድን ላይ ክስ ተመሠረተባቸው

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሰብኣዊ መብት ጥሰት ስዊድን ላይ ክስ ተመሠረተባቸው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዓለም ዐቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን (አርኤስኤፍ) የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ከሰሰ።

የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ድርጅት ክሱን ስዊድን ለሚገኘው ዐቃቤ ህግ ማቅረቡንም ይፋ አድርጓል።
ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተጨማሪ ሠባት ከፍተኛ ባለሥልጣናትንም በሰብዓዊነት ላይ በሚፈፀሙ ዓለም ዐቀፍ ወንጀሎች በቡድኑ ተወንጅለዋል።
ለኢሳያስ አፈወርቂ ክስ መነሻ የሆነው ለሁለት ዐሥርት ዓመታት በእስር ላይ የሚገኘው ኤርትራዊ-ስዊድናዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ ጋር በተያያዘ መሆኑም ታውቋል።
ባለሥልጣናቱ ጠንከር ያለ ምርመራ እንዲከፈትባቸው፣ ጋዜጠኛውን በማገት፣ በማንገላታትና ያለበትንም ደብዛ በማጥፋት ክስ  እንደሚመሠረትባቸው ነው የተነገረው።
ዳዊት ይስሀቅ በዓለም ላይ ለረዥም ዓመታት በእስር ላይ የሚገኝ ጋዜጠኛ እንደሆነም ቡድኑ በድኅረ ገጹ ያስነበበው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ድርጅት፤ ቡድኑን በመወከል ክሱን ያቀረቡት ሁለት ስዊድናዊ ጠበቆች እንደሆኑና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የፍትህና የማስታወቂያ ሚኒስትሮችና ሌሎች አራት ከፍተኛ ባለስልጣናት በክሱ ውስጥ እንዲካተት መደረጉን አስታውቋል።
“ባለሥልጣናቱ ምንም እንኳን ደረጃቸው ከፍ ያለ ቢሆንም ዳዊትን ይስሃቅን አስረው ለሀያ ዓመታት እንዲቆይ ያደረጉት ግለሰቦች ለወንጀላቸው ሓላፊነት ሊወስዱ ይገባል” በማለት በክሱ ላይ ፊርማቸውን ካስቀመጡት መሀል አንዱ ግለሰብ፤ “እነዚህ ግለሰቦች በፍፁም ማን አለብኝነት የፈለጉትን እንዲያደርጉና መክሰስ የሚችሉም አገራት ከተዋቸው ፍትህ በኤርትራ ሊሰፍን አይችልም” ሲሉ ተደመጠዋል።
ጋዜጠኛና ገጣሚ ዳዊት ይስሃቅ ነፃ ኤርትራን አገለግላሁ በማለት ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሶ የለውጥ ደጋፊ የሆነ ጋዜጣም አቋቁሞም የነበረ ቢሆንም፣ የኤርትራ መንግሥት የግል ጋዜጦችን ከመዝጋት ባሻገር የሚቀርቡበትን ትችት ዝም ለማሰኘት  በጀመረው ዘመቻም ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና ተማሪዎችን ለእስር ሲዳርግ እ.ኤ.አ 2001 ዳዊትን ጨምሮ አማኑኤል እስራት፤ መድህኔ ሃይሌ፣ የሱፍ መሐመድ አሊ፣ ማቲዮስ ኀብተአብንና ሌሎች በርካታ ጋዜጠኞችን ማሰሩ አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY