ሰቆቃ ወብልጽግና || ያሬድ ኃይለማርያም

ሰቆቃ ወብልጽግና || ያሬድ ኃይለማርያም

በዘመነ ብልጽግና በዘር እና በሃይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች የየዕለት ዜናዎች ሆነዋል። ባለፉት ሁለት አመታት በጅምላ ጭፍጨፋዎች ብቻ የተፈጸሙት ግድያዎች መጠን፤ የአገዳደል ጭካኔ ባህሪያቸው፣ ተደጋግመው የሚፈጸሙበት ፍጥነት፣ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ የሚደርሱት የጉዳት መጠን፣ ጥቃቶቹ በማንነት ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸው፣ በመንግሥት በኩል የሚታየው ከልክ ያለፈ ዳተኝነት እና ለጉዳቶቹ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን ሌሎች ከነዚህ የከፉ አደጋዎችን እንድንጠብቅ ማለማመጃ እየመሰሉኝ መጥተዋል።

ከመጀመሪያው የቡራዩ ጭፍጨፋ አንስቶ እስከዛሬው የጉራፈርዳ እልቂት እጅግ በርካታ የሆኑ ዜጎች ህይወት ለማየት እና ለመስማት በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ተቀጥፏል። አይተን እና ሰምተነው በማናውቀው ሁኔታ ዘግናኝ የጭካኔ አገዳደሎች ተፈጽመዋል። የወንዶችን አንገትና ብልት፣ የሴቶችን ጡት መቁረጥ፣ የሰዎችን ገላ መበለት፣ ከነነፍሳቸው አቃጥሎ እና ቆዳ ገፎ አሰቃይቶ መግደል፣ አስከሬን በየመንገዱ መጎተት፣ ለቀናት የገደሉትን ሰው ሜዳ ላይ ዘርግቶ እንዳይቀበር መከልከል፣ ቤት ሙሉ ሰው ሌሊት በተኙበት ከነቤታቸው በእሳት አንድዶ በጅምላ መግደል፣ እናትን ልጆቿና ባሏ ፊት በቡድን መድፈር፣ የሰው አንገት ቆርጦ አጥር ላይ ማንጠልጠል፣ እናትን ካዘለችው ህጻን ጋር በአንድ ቀስት ሰፍቶ መግደል፣ የሀይማኖት ተቋማትን ማቃጠል፣ በገጀራ እና ሚስማር በተሰካበት ቆመጥ የሰውን አናት አፍርሶ መግደል፣ ሴት ተማሪዎችን አፎኖ መሰወር እና ሌሎች ሰቆቃዎች በእነዚህ ሁለት አመታት ውስጥ አንዳንዴ በየወሩ፣ አንዳንዴም በየሳምንቱ የተለመዱ ክስተቶች ሆነዋል።

ይህ በሰቆቃ እና በፍጅት የተሞላው የብልጽግና ጉዞ በዚህ መልኩ ከቀጠለ በህውሃት ዘመን ከተፈጸመው የመብት ጥሰት ማስላቁ አይቀርም። ከሁሉም የሚያሳስበው እና የሚያስፈራው ከጥሰቶቹ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው እና ድርጊቱን በፍጥነት እንዲቆም ማድረግም ይሁን እንዳይፈጸም ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እየቻሉ ጏላፊነታቸውን ያልተወጡ ሹማምንት ዛሬም እንደ ህውሃቱ ዘመን ተጠያቂ አለመሆናቸው ነው። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ለተፈጸመው ዘር እና ጏይማኖት ተኮር ጥቃት በግንባር ቀደምነት ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው የክልሉ ፕሬዚደንት ኦቦ ሽመልስ አብዲሳ ይባስ ብሎ ባህር ዳር ላይ ካባ ሲጎናጸፉ ማየት culture of impunity – ከተጠያቂነት የማምለጥ ባህል ኢትዮጵያ ውስጥ ቀንድ ማብቀሉን እና እየደነደነም መሄዱን ጥሩ ማሳያ ነው።

ሕዝብ በግፈኞች እጅ ካለቀ፣ ከተሳቀቀ፣ ቅስሙ ከደቀቀ፣ ከተጎሳቆለ፣ ከተፈናቀለ፣ ከተራቆተ በኋላ ብልጽግናው ለማን ሊሆን ነው? ለመበልጸግ መኖር አይቀድምም ወይ? ለመኖር ሰላም እና የሕግ የበላይነት መስፈን ግድ አይልም ወይ? ሰላም እንዲሰፍን እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ቁርጠኛ እና ጠንካራ መንግስታዊ መዋቅር እንዲኖር ግድ አይልም ወይ? ሕዝብ ሲያልቅ አያገባንም ብለው ቤታቸው ገብተው የሰላም እንቅልፍ የሚተኙ ሹሞች በሞሉበት አገር መበልጸጉ ቀርቶ መክረምስ ይቻላል ወይ? ሰቆቃ ወብልጽግና …

LEAVE A REPLY