ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአዲስ አበባ ከተማ የ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርት የፊታችን ሰኞ እንደሚጀመር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ይፋ አደረገ።
በአንድ ክፍል 25 ተማሪዎች ርቀታቸውን ጠብቀው በፈረቃ እንደሚማሩ፣ አንድ ወንበር ለአንድ ተማሪ እንዲሆንም ቅድመ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የገለፁት የቢሮ ሓላፊው አቶ ዘላለም ሙላቱ፤ ፈረቃውና በአንድ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር በመንግሥትም በግል ትምህርት ቤቶችም ተመሳሳይ እንደሆነም አብራርተዋል።
በመንግሥት ትምህርት ቤቶች 2 ሺኅ 300 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ መጀመሩን እና
ኮቪድ-19 በተማሪዎች ላይ ስጋት እንዳያሳድር የለይቶ ማቆያ አገልግሎት ሲሰጡ በነበሩ ትምህርት ቤቶች ላይ የኬሚካል ርጭት መከናወኑም ታውቋል።
በመዲናዋ በሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል የትምህርት ቤት ክሊኒኮችን ለማቋቋም የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ያስረዱት ሓላፊው፤ ለዚህም የ2 ሺኅ 52 የጤና ባለሙያዎች ቅጥር በመካሄድ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
በሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የውሀ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ እንዲኖር 3 ሺኅ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከሮች የተሰራጩ ሲሆን፣ በመማር ማስተማር ሂደቱ የመምህራን እጥረት እንዳይኖር ቅጥር እየተፈፀመ ከመሆኑ ባሻገር የመጽሐፍ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ መሟላቱን፤ የተማሪዎች ምገባም ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እንደሚከናወን ተሰምቷል።
የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ፣ ሳኒታይዘርና የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች በከተማ አስተዳደሩ ሥር ለሚገኙ 513 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መዳረሳቸው የገለጸው የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ፤ የግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚውሉ ግብዓቶችን ጨምሮ ሁሉንም መሣሪያዎች ከተማሪዎች ወላጆች ጋር በመነጋገር በራሳቸው የሚያሟሉ እንደሆነ አስታውቋል።