ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለዶናልድ ትራምፕ አስተያየት ምላሽ ሰጡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለዶናልድ ትራምፕ አስተያየት ምላሽ ሰጡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያ ሕይወታቸውን ሰጥተው ሊታዘዟት በተዘጋጁ ልጆቿ እንጂ፣ ጥቂት ሰጥተው ብዙ ሊያዝዟት በሚሞክሩ ተማምና እንደማታውቅ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በፌስቡክ ሰሌዳው ይፋ ያደረገው መግለጫ በይፋና በስም ባይጠቅሰውም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለተናገሩት ንግግር የተሰጠ ምላሽ መሆኑ ተገምቷል።
ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ ታምና በሕዝቧ አንድነትና ጽናት የቆመች ሀገር ናት ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት፣ “የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ግድብ ነው። ኢትዮጵያውያን አሰቡት፤ ኢትዮጵያውያን ጀመሩት፤ ኢትዮጵያውያን ገነቡት፤ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ይጨርሱታል፤ አይቀሬ ነው” ሲል መላውን ኢትዮጵያዊ ያነቃቃ መግለጫ ሰጥቷል።
“ኢትዮጵያን የፈጠራት አምላኳ ነው። የገነቧት ደግሞ ልጆቿ ናቸው ። ኢትዮጵያ ልጆቿ በከፈሉት መስዋዕትነት ዓለምን ጉድ ያሰኙ ታሪኮችን ሠርታለች፤ እነዚህን አስደናቂ ታሪኮች ስትሠራ አብረዋት ታሪክ የሠሩ ወዳጆች ነበሯት፤  የከዷት ወዳጆችም ነበሩ፤ ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም” ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፤ ” ዓለም ታሪክ ያረጋገጣቸው ሁለት ሀቆች አሉ ፣ ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ የለም የሚለው ቀዳሚው ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለአንድ ዓላማ ከቆሙ፣ ድል ማድረጋቸው አይቀርም የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ነው” ብሏል።
“የሚያዋጣን ኅብረት አንድነታችን ነው። ለእኛ ያለነው እኛ መሆናችንን አውቀን ስለ እኛ ጉዳይ እኛው እራሳችን ኢትዮጵያን አለንልሽ እንበላት። ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ለኢትዮጵያ እንቁም። ከባዱ ፈተና ከውጭ የሚመጣው አይደለም። ከባዱ ፈተና ተለያይተን ችግሩን ከተጋፈጥነው ነው” ሲል የሀገሪቱን አቋም ይፋ ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በስተመጨረሻ፤ “ማንም ገዝቶን አያውቅም፤ ወደፊትም ማንም አይገዛንም። ታሪክ የሠሩ እጆች ዛሬም አሉ፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸውን ለማክበር እንጂ ጠላቶቻቸውን ለመታዘዝ ተንበርክከው አያውቁም፤ ዛሬም ወደፊትም አናደርገውም” ሲል አሳስቧል።

LEAVE A REPLY