ቅዱስ ሲኖዶስ ትራምፕ ያስተላለፉትን መልእክት አወገዘ

ቅዱስ ሲኖዶስ ትራምፕ ያስተላለፉትን መልእክት አወገዘ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፤ የኢትዮጵያን ሰላምና ጥቅም ሊያሳጣ በሚችል መልኩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያስተላለፉትን የጦርነት ጥሪ አወገዘ።

በሀገራችን ኢትዮጵያ የሕዝባችንን የዘመናት ድሕነት እና የኑሮ ጉስቁልና አስወግዶ ለኢትዮጵያ ብልጽግና ያመጣል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፤ ሥራው ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ደረጃ ላይ መድረሱን ያስታወሰው የቄዱስ ሲኖዶስ መግለጫ፤ የግድቡ የዕለት ከዕለት ሥራ እየተከናወነ ፣ ሕዝባችንም የተለመደ ድጋፉን እያደረገ ከሦስት ዓመታት በኋላ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ ጥለንበታል ብሏል።
“ኢትዮጵያውያን በተስፋ ፣ በገንዘብ፣ በጉልበትና በሙያው የበኩሉን ድጋፍ በማበርከት እየተረባረቡ ባለበት ወቅት ይህን መሰል ንግግር መምጣቱ ያሳዝናል”  ቅዱስ ሲኖዶስ፤
ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ታፍራ እና ተከብራ የኖረችው፣  ለመላው ጥቁር ሕዝብ ምሳሌ ለመሆን የበቃችው፣ ሀገሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር፣ ሕዝቡም ሕዝበ እግዚአብሔር በመሆኑ ነው ሲል በመግለጫው ላይ ሀቁን ይፋ አድርጓል።
“ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሆነ ከሌሎች ተመሳሳይ አካላት በኢትዮጵያ ላይ እየተላለፈ ያለው የጥፋት ጥሪ መተዛዘቢያ ከመሆን በስተቀር ሀገራችን ጠባቂዋ በሆነው እግዚአብሔር እና በሕዝባችን አንድነት ተከብራ እና ተጠብቃ እንደምትኖር ሙሉ እምነታችን ነው”  ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፤
መላው የዓለም መንግሥታት እና ሕብረተሰብ ችግሩን በጥልቀት እንዲገነዘቡትም መልእክት አስተላልፏል።
በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ የፌዴራል እና የክልል መሪዎች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የትኛውንም የግል እና የቡድን አመለካከት ወደ ጐን በመተው አንድነታቸውን በማጠናከር ለሀገር ሕልውና እንዲቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

LEAVE A REPLY