በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሱ ኹከቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች እርዳታ የሚውል 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን...

በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሱ ኹከቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች እርዳታ የሚውል 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ተሰበሰበ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በተለያዮ ጊዜያት በኦሮሚያ ክልል ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶችና ኹከቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ የሚውል 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ተሰበሰበ።

የክርስቲያን በጎ አድራጎት ልማት ማኅበራት ሕብረት (CCRDA)  እንደገለጸው ከሆነ ገንዘቡ የተሰበሰበው በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ለተፈናቀሉና ዜጎች ድጋፍ እንዲውል ነው።
የሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት አሜሪካ ከሚገኙ አብያተ ክርስትያናት፣ እንዲሁም በመላው አውሮፓ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያሰባሰበውን 2 ነጥብ 3 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለክርስቲያን በጎ አድራጎት ልማት ማኅበራት ሕብረት  እንዳስረከበም አስታውቋል።
የተሰበሰበው ገንዘብ በተለይ በምዕራብ አርሲ፣ በምዕራብ ሐረርጌ፣ በምስራቅ ሐረርጌ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ አርሲ፣ ባሌ፣ ሻሸመኔ እና ዝዋይ ከተሞች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየእምነት ተቋማት ተጠልለው ለሚገኙ ምዕመናን እንደሚከፋፈል ከመግለጫው መረዳት ተችሏል።
የክርስቲያን በጎ አድራጎት ልማት ማኅበራት ሕብረት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ንጉሡ ለገሰ 2 ሺኅ 170 የሚሆኑ አባዎራዎች በሚቀጥሉት ሥድሥት ወራት ሙሉ ለሙሉ የገንዘብ ድጋፉ እንደሚደርሳቸው ጠቁመው፤ ከእነርሱ በተጨማሪ በኮፈሌ ከ8 ሺኅ በላይ ምዕመናን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የሚገኙ በመሆኑ፣ መልሶ የማቋቋም ሥራ እንዲሠራ በመላው ዓለም የሚገኙ ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አድርገዋል።

LEAVE A REPLY