ጃዋር መሐመድ አብረውት ብዙ የሠሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት የባንክ አካውንት አለመታገዱን አጋለጠ

ጃዋር መሐመድ አብረውት ብዙ የሠሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት የባንክ አካውንት አለመታገዱን አጋለጠ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዛሬ የተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ የተደረገባቸው ተከሳሾች ጉዳይን ሲመለከት ዋለ።

ከዘጠኙ  የነጃዋር ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ቶኩማ ዳባ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ የተደረገባቸው ተከሳሾች ዝርዝር ወጪያቸው ምን ያክል እንደሆነ በጽሑፍ ለፍርድ ቤት አቅርበዋል።
ጠበቃው ተከሳሾቹ ለቀለብ፣ የቤት ኪራይ እና የባንክ እዳ ለመክፈል እና ሌሎች ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን እንዲቻላቸው እግዱ እንዲነሳላቸው ፍርድ ቤቱን በድጋሚ ከመጠየቃቸው ባሻገር፤ ብዙዎች በጽንፈኝነት የሚፈርጁት
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ንብረት ላይ የተጣለው እግድም በተመሳሳይ እንዲነሳ ጥያቄ አቅርበዋል።
የተከሳሾቹ ጠበቆች ያቀረቡት የወጪ ዝርዝር በማስረጃ የተደገፈ አይደለም፤ የኦኤምኤን ንብረትም መመለስ የለበትም ሲል የተከራከረው ዐቃቤ ሕግ የእግዱ መነሳት ከጠቃሚነቱ ይልቅ ጎጂነቱ ያመዝናል ሲል ተከራክሯል።
 “ከእኔ ጋር ለአንድ ቀን ሻይ የጠጡ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው ታግዷል፤ ብዙ ነገር አብሬ የሠራሁት የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን የባንክ ሂሳባቸው አልተዘጋባቸው፣ እንዴት ሕጉ ለእነርሱ አይሠራም?” ያለው ጃዋር መሐመድ፤ በፍርድ ቤቱ የእግድ ውሳኔ ላይ ቅሬታ እንዳለው አስረድቷል።
ከመኖሪያ ቤቴ የተወሰደው ንብረት ሥርዓትን ተከትሎ ተመዝግቦ የተወሰደ ሳይሆን፣ ዘረፋ ነው የተፈጸመብኝ  የሚለው ጃዋር መሐመድ፤ “መኖሪያ ቤቴ ውስጥ ከ100 ሺኅ ብር በላይ፣ ወርቅ፣ የእጅ ሰዐት እና በሽልማት ያገኘኋቸው የተለያዩ ሜዳሊያዎች ፖሊስ ወስዶ የራሱ ንብረት አድርጎታል። ለምንድነው የምዘረፈው” በማለትም በፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል
ሌላኛው ተከሳሽ አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው ተሸከርካሪን ጨምሮ ንብረታቸው ላይ የተላለፈው እግድ ከሕግ ውጪ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ “እኔ ለ37 ዓመታት የመንግሥት ሠራተኛ ሆኜ የሠራሁ ሰው ነኝ። ይህን ያክል ዓመት የሠራ ሰው እንዴት አሮጌ መኪና ይኖረዋል? ማለት ትክክል አይደለም። ወደ አዳማ እና ነቀምቴ በሄድኩ ጊዜ ሕዝቡ ምን ዓይነት አቀባበል እንዳደረገልኝ ታውቃላችሁ። ወደ ውጪ በሄድኩ ጊዜም መኪና ተሸልሜ ነበር። ይህችን አሮጌ መኪና ንብረት አፈራ ተብሎ ማገዱ ትክክል አይደለም” ብለዋል።
በስተመጨረሻ ችሎቱ በጉዳዮ ላይ የዐቃቤ ሕግን መልስ ለመስማት ለጥቅምት 24 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

LEAVE A REPLY