የደምቢዶሎ ተማሪዎችን በማገት የተጠረጠሩት 17 ግለሰቦች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

የደምቢዶሎ ተማሪዎችን በማገት የተጠረጠሩት 17 ግለሰቦች የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || እስካሁን ደብዛቸው ያልተገኘው የደምቢዶሎ ተማሪዎችን አግተዋል በሚል የተጠረጠሩት 17 ግለሰቦች ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደረገ።

ዐቃቤ ሕግ በእነ ከሊፋ አብዱራህማን በሚጠራው የክስ መዝገብ በ17 ግለሰቦች ላይ በህዳር 24 እና 25 ቀን 2012 ዓ.ም ከአማራ ክልል የሄዱ ተማሪዎችን በመለየት ማገታቸውን ጠቅሶ፣ የፀረ ሽብርተኝነትን አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3/3 በመተላለፍ እንደ ወንጀል ተሳትፏቸው ሦስት ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የሕገ መንግሥትና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ከሊፋ አብዱረህማንን ጨምሮ ዘጠኝ ተከሳሾች ዛሬ የቀረቡ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ ወደ ቤተሰብ እየተመለሱ የነበሩ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን መታወቂያቸውን በመለየት፣ ከተሳፈሩበት ተሽከርካሪ በማስወረድ አግተው አሳልፈው ለኦነግ ሸኔ በመስጠት፣ እንዲሁም በወቅቱ ተሽከርካሪ በማሽከርከርና በረዳትነት ሢሠሩና ለወንጀሉ በመተባበር መረጃውን ከፀጥታ አካል ደብቀዋል የተባሉ ግለሰቦች ላይ ሦስት ክስ ዐቃቤ ሕግ ማቅረቡ አይዘነጋም።
ሆኖም ይህ ክስ አጠቃላይ የሽብር አዋጁን ማቋቋሚያ ፍሬ ስለማያሟላና የተጠቀሰው አዋጅና ድንጋጌዎች ስለማይጣጣሙ 1ኛው ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ይደረግልን ሲሉ መቃወሚያ አቅርበው ነበር።
በዚህ መሠረት ክስ የመሠረተው ዐቃቤ ሕ የኦነግ ሸኔ የፖለቲካ ወይም የርዮተ ዓለም ዓላማቸውን ለማራመድ፣ ሕዝብን ለማሸበር ወይም መንግሥትን ለማስገደድ በማሰብ የወንጀል ድርጊት በሚሰጠው ውጤት ተካፋይ በመሆን እና የራሳቸው በማድረግ በቀጥታ በመፈጸም እና ወንጀሉን ለመፈጸም ቅድመ ዝግጅት በማድረግ በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወስጥ የተፈጠረውን የተማሪዎች ግጭት በመፍራት፤ ወደቤተሰቦቻቸው ሲያቀኑ የነበሩ የአማራ ከልል ተማሪዎችን ያገተበት መንገድ በፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 የተመለከተውን የሕጉን ፍሬ ነገር የሚያሟላ በመሆኑ በተከሳሾች የቀረበው መቃወሚያ ውድቅ ይደረግልኝ” ሲል በጽሁፍ ምላሽ  መስጠቱን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል።
ተከሳሾች “ክሱ የቀረበው በተሻረ አዋጅ በመሆኑ ክሱ መቅረብ ያለበት በአዲሱ አዋጅ መሰረት ነው” በሚል ቢከራከሩም ፍርድ ቤቱ መቃወሚያቸውን በማድረግ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት 25 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።

LEAVE A REPLY