ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ዋናውን ድርድር በሳምንት ውስጥ ለማከናወን ከስምምነት ደረሱ

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ዋናውን ድርድር በሳምንት ውስጥ ለማከናወን ከስምምነት ደረሱ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በሠባት ቀናት ውስጥ የሦስትዮሽ ድርድሩን ለማካሄድ በቀጣይ የድርድሩን አካሄዶች እና የጊዜ ሰሌዳ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል መግባባታቸው ተሰማ።

ሦስቱ ሀገራቱ በሠባት ቀናት ውስጥ ድርድሩን ሲያካሂዱ በቀጣይ የድርድሩ አካሄዶች እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ ስምምነት መድረስ፣ ልዩነት ባሏቸው ጉዳዮች ዙሪያ ልዩነትን ለማጥበብ እና ውጤቱንም ለውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቀጣይ ስብሰባ ለማቅረብ መግባባት ላይ ደርሰዋል ነው የተባለው።
የደቡብ አፍሪካ የዓለም ዐቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ሕብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የውጭ ጉዳይ እና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጥቅምት 17 ቀን(ትናንት) 2013 ዓ.ም በበይነ-መረብ ስብሰባ ማካሄዳቸውን አስታውቀዋል።
ጉዳዮን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጋራ ባወጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሰፈረው ከሆነ፤ ስብሰባው በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ሥር እየተካሄደ ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የተመለከተው የሦስትዮሽ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መክሯል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ቀደም ብሎ በጥቅምት መጀመሪያ ከኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መሪዎች ጋር በስልክ ባደረጓቸው ውይይቶች በተደረሰው መግባባት እና ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ድርድሩን ለመቀጠል ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የቴክኒክ ስብሰባም በሱዳን የውሃ ጉዳይ ሚኒስትር ሰብሳቢነት ይከናወናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

LEAVE A REPLY