በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር ሕክምና የሚሰጡ ሥድሥት የጤና ተቋማት እየተገነቡ ነው ተባለ

በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር ሕክምና የሚሰጡ ሥድሥት የጤና ተቋማት እየተገነቡ ነው ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሥድሥት የጡት ካንሰር ሕክምና የሚሰጡ የጤና ተቋማት ግንባታ ሥራ እየተካሄደ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ዛሬ በተከናወነው ዓለም ዐቀፍ የጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ወርን በማስመልከት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ፤ ኅብረተሰቡ ስለጡት ካንሰር ያለው ግንዛቤ ሊያድግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በዓለም ላይ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ሴቶች በየዓመቱ በጡት ካንሰር እንደሚያዙ፣ በኢትዮጵያም በካንሰር ከሚያዙ ሰዎች መካከል ሲሶ የሚሆኑት የጡት ካንሰር ሕሙማን መሆናቸውን የጠቆሙት ዶክተር ሊያ፤ የጡት ካንሰር ሕመም ግንባር ቀደም ገዳይ በሽታ ለመሆን የቻለው አብዛኛው የጡት ካንሰር ሕሙማን ወደ ጤና ተቋማት ዘግይተው መሄዳቸው በቀዳሚ ምክንያትነት ይቀመጣል ብለዋል።
የዚህ ምክንያት በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆንና በተለይ ለካንሰር ሕሙማንን አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማት እጥረት ተጠቃሽ  እንደሆነ ያብራሩት የጤና ሚኒስትሯ፤ ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል ሚኒስቴሩ የጡት ካንሰር ሕክምናን ተደራሽነት ለማስፋት የሚያስችሉ 12 የክልል ሆስፒታሎች የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ሕክምናውን እንዲሰጡ መደረጉን ገልጸዋል።
በዚህ አሠራር በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ለጡት ካንሰር ሕክምና የሚያስፈልገውንና ከዚህ ቀደም ሥድሥት ወር የነበረውን ጊዜ ወደ ሁለት ሳምንታት ዝቅ እንዲል ማድረግ ተችሏል ነው የተባለው።
በአሁኑ ወቅት በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ ክልሎችና በአዲስ አበባ ተጨማሪ ሥድሥት የጡት ካንሰር ሕክምና የሚሰጡ ተቋማት በግንባታ ሂደት ላይ ናቸው ያሉት ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ከእነዚህም መካከል ሦስቱ በመጪዎቹ ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩና ቀሪዎቹም በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ ይፋ አድርገዋል።

LEAVE A REPLY