ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ስም የተሰየመው የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ሰያሜ ሊቀየር መሆኑ ታወቀ።
በቀድሞው የህወሓት ሊቀ መንበር ስም መጠሪያ የተሰጠው የእዚህ ተቋም የቦርድ ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ናቸው። በመንግሥት ተቋምነት ወደ ሥራ የገባው መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ስያሜው ሊቀየር እንደሆነ ከተቋሙ ሠራተኞች የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህ ባሻገር የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ የአካዳሚውን ተልዕኮ የሚመጥን ስያሜ ለመስጠትም ስራ ሲሰራ እንደነበር መግለጹን የዘገበው አል ዐይን ኒውስ፣ እስካሁን መለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ሲባል የነበረው የመንግስት ተቋም “የኢትዮጵያ አመራር አካዳሚ” እንዲባል ሀሳብ መቅረቡን ተከትሎ በቀጣይ ይህ መጠሪያ እውን ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
የተቋማት ስያሜ የራሳቸው የሆኑ ሳይንሳዊ መስፈርቶችን በመከተል የሚሰጥ መሆኑን የተናገሩት የሪፎርሙ ቴክኒካል ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን አረጋ፤ ከአካዳሚው ጋር ተመሳሳይ ተልዕኮ ያላቸውን 19 ተቋማትን ከተለያዩ ሀገራት በመለየትና በመውሰድ ስያሜያቸውን የማጥናት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
ከዚህ አኳያ ከ8 እስከ 10 የሚደርሱ ዓለም ዐቀፍ መስፈርቶችን በማስቀመጥ አካዳሚው ሊኖረው የሚገባው ስያሜ ላይ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተከትሎ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ፤ ለስያሜው በቀረቡት አማራጮች ላይ ውይይት ተደርጎበት ሀገርን የሚወክል ስያሜ መሆን አለበት የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት እንዳገኘም ሓላፊው ከወዲሁ ጠቁመዋል።
የተቋሙ ስያሜ ሁሉን ዐቀፍና አብዛኛውን የሚያስማማ እንዲሆን መታመኑን የገለጹት አቶ ጥላሁን የስም ለውጥ ሀሳቡም ለጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ ቤት እንደቀረበና በቅርቡም ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የለውጡ ቡድን አጋፋሪና የብአዴን ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ዮሐንስ ቧያለው የካቲት 2012 ዓ.ም የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሾሙ፤ “አሁን ተቋሙ ባለው የሕዝብ አመለካከት በተቋሙ መሥራት የምችልበት ሁኔታ ስለሌለ የቀረበውን ሹመት ለመቀበል ያስቸግረኛል” በሚል ከስያሜው ጋር በተያያዘ ሓላፊነቱን አልቀበልም ማለታቸው አይዘነጋም።