ኢትዮጵያ ነገ ዜና || 1 ሺኅ 495ኛው የመውሊድ በአል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ ጥቂት የእምነቱ ተወካዮችን ብቻ ባካተተ መልኩ በታላቁ አንዋር መስጅድ ተከበረ።
በመውሊድ በዓል ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር እድሪስ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም በርካታ የሃይማኖቱ አባቶች ታዳሚ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ቀኒ ነብዩ መሐመድ የተወለዱበት በመሆኑ በፆም፣ በዱአ፣ እንዲሁም በአንድነት ልናከብረው ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።
ነብዩ መሀመድ አንድነትን እና ሰላምን ያስተማ፣ ለሰው ልጆች እዝነትን ያመጡ መሆናቸውን ያስታወሱት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ የነብዩን ሥራ መሪ አድርገን ለሀገራችን ሰላም ለሕዝባችንም አንድነት ልንቆም ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ሃይማኖት፣ ብሄር እና ሕዝቦች መኖሪያ እንደመሆኗ ሕዝበ ሙስሊሙ ለከተማችን ሰላም ስላደረገው አስዋፅዖ ከልብ እናመሰግነዋለን ሲሉ ተናግዋል።