ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የብሔርተኝነት ስሜትና ፖለቲካው በእጅጉ በገዘፈባቸው የአማራና ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ጀምረዋል።
በተጀመረው የውይይት መድረክ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊዎች ናቸው ቢባልም እሰካሁን ድረስ የትኞቹ ፓርቲዎች ተገኝተው የትኞቹ እንዳልተሳተፉ በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።
የምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና የምክክር ባህል ማጎልበት ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ውይይቱ ዛሬ ቢጀምርም እሰከ ነገ የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል።
በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ከወዲሁ ተገልጿል። የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ፣ የሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት፣ የሀገር ግንባታ ድርሻ፣ ሰላማዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ላይም በዋናነት ትኩረት እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
የሁለቱ ክልሎች ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው የነገሥታት፣ የወታደራዊ ደርግ፣ ኢሕአዴግ፣ የለውጥ ጉዞና የወደፊት የፖለቲካ አቅጣጫ ላይም ምክክር ያደርጋሉ ነው የተባለው።