ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአትዮጵያ አየር መንገድ የ2020 ምርጥ የአፍሪካ የጭነት አየር መንገድ ሽልማት አሸናፊ መሆኑ ተነገረ።
አየር መንገዱ ቤስት ካርጎ ኤርላይን የተሰኘውን ሽልማት ያገኘው ዘርፉ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጎዳበት ጊዜ የካርጎ አገልግሎትን በስኬት በማከናወኑ እንደሆነም ተገልጿል።
የአቬሽን ዘርፉ ተዋናዮች ከክስረት ለመዳን በሚጥሩበት በዚህ አስቸጋሪ ዓመት ለሽልማት እንዲበቃ አመራሩና ሠራተኞቹ ላበረከቱት አስተዋፅዖ አየር መንገዱ ምስጋናውን በይፋ አቅርቧል።
“ለብዙ አየር መንገዶች የክስረት ምንጭ የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ እኛ ፊታችንን ወደ ጭነት ማመላለስ እንድናተኩር በማድረጉ ለዚህ ሽልማት አብቅቶናል” ሲልም ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስኬቱን ምንጭ በግልጽ አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጀምሮ ለአፍሪካም ሆነ ለሌላው የዓለም ክፍል የሕክምና ቁሶችን ለማዳረስ በሙሉ አቅሙ ወደ ካርጎ አገልግሎት ገብቶ ለወራት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ አይዘነጋም።