የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከነገ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል ተባለ

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከነገ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከነገ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረጉ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ይፋ አደረገ።

በዛሬው እለት ቱሪዝም ኢትዮጵያ በአማራ ክልል የላልይበላ ከተማ በቱሪዝም ዘርፍ ለተሠማሩ ባለድርሻ አካላት በጎብኚዎች ደህንነት አጠባበቅ፣ ለቱሪስት መረጃ አሰጣጥና በሀገር  ዐቀፍ የቱሪዝም መለያ (ብራንድ) ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል።
ሥልጠናው ከጎንደር፣ ባህርዳር፣ ላሊበላና ደባርቅ አካባቢ ለተወጣጡ ከ600 በላይ አስጎብኚዎች፣ የሆቴል ባለቤቶች፣ ድጋፍ ሰጪዎችና የደህንነት ጠባቂዎች መሆኑ ታውቋል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ስለሺ ግርማ እንዳሉት የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከነገ ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት የሚደረጉ ሲሆን፣ ላልይበላ ለጎብኝዎች ክፍት መደረጉን ተከትሎ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች የሚገኙበት የተለያዩ ዝግጅቶች ያሉበት መርሃ ግብር እንደሚከናወንም ተሰምቷል።
በተያያዘ ዜና በአማራ ክልል የጎንደር ቤተ መንግሥት፣ ጢስ አባይ እና የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከጥቅምት 15 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለጎብኚዎች ክፍት መደረጋቸው ታውቋል።
በአማራ ክልልና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየተከፈቱ ያሉት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መመሪያን በተከተለ መልኩ በመሆኑ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንደሚደረግም ተገልጿል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የቱሪዝም ዘርፉን ክፉኛ እንደጎዳውና በዚህም ምክንያትም በዘርፉ ተሠማርተው የነበሩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ያለ ሥራ ለረጅም ጊዜያት እንዲቀመጡ መገደዳቸውን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤
በሀገር ደረጃም ከቱሪዝም ዘርፍ ለማግኘት የታቀደው ገቢ ሳይሳካ መቅረቱን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ዘርፉን ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አስጎብኚዎች በአካባቢያቸው የሚገኙ ቅርሶችና መስህቦችን ከማስጎብኘት በተጨማሪ ኢትዮጵያ በሰው ዘር መገኛ፣ ጥንታዊ ባህል ያላት፣ የቡና መገኛና በሌሎችም ቀደምት ሀገር መሆኗን ማስተዋወቅ ይገባቸዋል ብለዋል።

LEAVE A REPLY