ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያዊው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም በቅርቡ ከእርሳቸው ጋር ንክኪ የነበረው ግለሰብ በኮሮናቫይረስ መያዙን ተከትሎ ራሳቸውን እንዳገለሉ ይፋ አደረጉ።
እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የበሽታው ምልክት እንደማይታይባቸው የተናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤
”በኮቪድ-19 መያዙ ከተረጋገጠ ግለሰብ ጋር ንክኪ እንዳለኝ ታውቋል። በጥሩ ጤንነት ላይ ነው የምገኘው፤ ምንም የቫይረሱን ምልክቶችም እያሳየሁ አይደለም። ነገር ግን በዓለም ጤና ድርጅት መመሪያዎች መሰረት ለሚቀጥሉት ቀናት ራሴን አግልዬ እቆያለሁ። ሥራዬንም በቤቴ እራለሁ” ብለዋል።
”እኔ እና የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረቦቼ የሰዎችን ሕይወት ለማዳንና ተጋላጭ የሆኑትን ከቫይረሱ ለመከላከል አብረውን ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር ያለንን የትብብር ሥራ እናስቀጥላለን” በማለት በቲውተር ገጻቸው ላይ መልእክት ያሰፈሩት ቴዎድሮስ አድኃኖም፤ ‘ሁሉንም የጤና መመሪያዎች መከተል የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የ55 ዓመቱ የቀድሞ የህወሓት ሥራ አስፈጻሚ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የጤና ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም፤ የኮቪድ-19 ስርጨት ሰንሰለትን መስበር የምንችለው በዚህ መንገድ ነው፣ ይህንን ካደረግንም ቫይረሱን እናሸንፈዋልን፤ የጤና ሥርዓታችንንም እንከላከለዋለን በማለት ያለቸውን ተስፋ አስቀምጠዋል።