ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአማራ ብሔር ላይ ዘር ተኮር በሆነ መልኩ እየተፈፀመ ያለው ጥቃት በመግለጫ የሚሽሞነሞን ሳይሆን የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሕግ አማካሪ መርሃፅድቅ መኮንን ተናገሩ።
የተፈጸመውና እየሆነ ያለው ጥቃት የንፁሀን ህልፈት እየተባለ የሚሽሞነሞን ሳይሆን ፤ በዓለም ዐቀፍ ሕግ ይቅርታ እና ምህረት እንኳን የማያሰጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሆነ ነው የሕግባለሙያው የገለጹት።
በሰሞነኛ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ዙሪያ ከአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ መርሀፅድቅ፤ “ይህንን በድፍረት ለመናገር በመንግሥት አካላት ላይም ድፍረቱም የለንም፤ ከፍተኛ የሆነ የወንጀል ጥቃት እየደረሰ ነው፤ የተደራጀ ወንጀል እየተፈጸመ ነው፤ ድርጊቱን በስሙ የመጥራት ድፍረት ሊኖረን ይገባል” ሲሉም እየተደብሰበሰ ያለው የዘር ተኮር ጥቃትን መጋፈጥ እንደሚገባ ይፋ አድርገዋል።
ድርጊቱን ማንም ይፈፅም ማን ኃላፊነቱን የሚወስደው በዚያ አካባቢ የሚገኘው የመንግሥት አካል ነው በማለት ለሟቾቹ ተጠያቂው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት መሆኑን የተናገሩት የሕግ ባለሙያው፤ በአካባቢው የሚገኝ የፀጥታ አካል፣ ደኅንነት፣ የመከላከያ ሠራዊት እና ወታደራዊ ኃይል እነዚህን ጥቃቶች መከላከል ካልቻለ የመንግሥትን እና የዜጎችን ኅልውና መታደግ አይችልም ሲሉ አስምረውበታል።
የሕግ አስከባሪ አካላት ራሳቸው ምን ያህል ከችግር የፀዱ ናቸው የሚለው ጉዳይም አነጋጋሪ እንደሆነ የጠቆሙት ሓላፊው መንግሥት በእነዚህ አካል ላይ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።