ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ትናንት ይፋ በተደረገው የ32 ሰዎች ሕልፈት በተጨማሪ ዛሬ ሁለት ሰዎች መሞታቸው በመረጋገጡ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ በተፈፀመው ጥቃት የሟቾች ቁጥር 34 መድረሱ ተሰማ።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዛሬ እንደገለፀው ከሆነ በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና ሲከታተሉ ከነበሩ 10 ሰዎች ውስጥ የ2 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዛሬ ጠዋት መረጃው ደርሶኛል ሲል ይፋ አድርጓል።
ይህንን ተከትሎም የሟቾች ቁጥር 34 መድረሱን የቢሮው ሐላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ አረጋግጠዋል። እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በዶክተር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የሟቾቹ ቁጥር ከተባለው በላይ መሆኑን ሲናገር፤ የዐይን እማኞች ደግሞ ወደ 60 እንደሚጠጋ ጠቁመዋል።
የጥቃቱ ፈፃሚዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ በ3 አቅጣጫ የፀጥታ ኃይሎች ተሠማርተዋል ያሉት አቶ ጌታቸው በቁጥር ባይገልፁትም በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች እንዳሉም ገልጸዋል።