ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ የደህንነት ስጋት አለን በሚል ምክንያት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ መቅረታቸው ታወቀ።
ዛሬ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት የተከሳሾች የንብረት እግድ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ የነበረው ቢሆንም ከተከሳሾች መካከል አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤት ሳይገኙ ቀርተዋል።
በቀጠሮው ሥራውን ያካሄደው ፍርድ ቤቱ አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ለምን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ሲጠይቅ፤ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ተከሳሾቹ የደህንነት ስጋት አለብን በሚል ምክንያት መቅረታቸውን ተናግረዋል።
“አሁን ባለው ሁኔታ አይደለም ጉዳት ይቅርና ሙከራ የግድያ ሙከራ ቢደረግብን ሀገሪቱ ወደ ከፋ አደጋ ውስጥ ስለሚያስገባት ለሀገሪቱ በማሰብ ወደ ፍርድ ቤት ከሚደረግ ጉዞ እራሳችንን ቆጥበናል” ማለታቸውንም በችሎቱ የተገኙት ሌላኛው ተከሳሽ አቶ ሐምዛ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።
በተጨማሪም አሁን ሀገሪቱ ውጥረት ውስጥ እያለች በንብረት ጉዳይ ላይ ለመከራከር ፍርድ ቤት መመላለስ ለእኛ ሃፍረት ነው በሚል ምክንያት ፍርድ ቤት አልቀረቡም ያሉት ሐምዛ ቦረና ፤ ጀዋር እና በቀለን ወክለው ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ይህን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ በንብረት እግዱ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሕዳር 15 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ተሰምቷል።