ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተማሪዎች ቅበላን ላልተወሰነ ጊዜ አራዘሙ።
አምቦ፣ ባህር ዳር ፣ ደብረ ማርቆስና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ላልተወሰነ ጊዜ እንደማይቀበሉ ካስታወቁት ዮንቨርስቲዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
በተመሳሳይ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ባወጣው አስቸኳይ ማስታወቂያ ተመራቂ ተማሪዎች ጥቅምት 27 እና 28 2013 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲገቡ ጥሪ ማስተላለፉን አስታውሶ፤ ሆኖም አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ጥሪ የተደረገላችሁ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች በአዲስ ማስታወቂያ ጥሪ እስከሚተላለፍ ድረስ ባሉበት እንድትቆዮ ሲል አሳስቧል።
አምቦ ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ ጥቅምት 25 እና 26 2013 ዓ.ም ተጠርተው የነበሩ ተማሪዎችን “በተፈጠረው አሁናዊ ሁኔታ የትራንስፖርት ችግር መፈጠሩን ተረድተናል። በመሆኑም በያላችሁበት ቆዩ” በማለት አሳስቦ፤ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው መድረስ ከቻሉ ግን ተማሪዎችን እንደሚቀበልም ጠቁሟል።
ወራቤ ዩኒቨርሲቲ ጥቅምት 30/ 2013 ዓ.ም ተማሪዎችን የመቀበል ጥሪ አስተላልፎ እንደነበረ አስታውሶ፤ የምዝገባ ፕሮግራሙ የተለወጠ እና ላልተወሰነ ግዜ የተራዘመ መሆኑን ገልጿል። “ተመራቂ ተማሪዎች አሁን ካለው ሀገራዊ ሁኔታ አንፃር ለደህንነታችሁ ባላችሁበት እንድትቆዩ” ሲል ያሳሰበው ደግሞ የአማራ ክልሉ ደብረማርቆስ ዮንቨርስቲ ነው።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ፤ በሀገሪቱ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ የተማሪዎችን እንቅስቃሴ መገታቱን ባስታወቀበት መግለጫ፤ በተመደቡበት ዮንቨርስቲ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች በግቢያቸው እንዲቆዩ እና በየግቢያቸው የሚሰጧቸውን ማሳሰቢያዎችም እየተከታተሉ እንዲንቀሳቀሱም አሳስቧል።