የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሥድሥት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሥድሥት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ

PM Netanyahu addressing the Ethiopian parliament

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ለሥድሥት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን ገለፀ።

የኢፌዲሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ፣ ጥቅምት 25/2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ መንግሥት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።
 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለሥድሥት ወራት ተፈጻሚ እንደሚሆን የጠቆመው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ፤ ይህንን አዋጅ የሚያስፈፅም በኢፌዲሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ አባላት ያሉት ግብረኃይል እንደተቋቋመም ይፋ ተደርጓል።
ግብረኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ሀይል” የሚል መጠሪያም ተሰጥቶታል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መደንገግ ያስፈለገበት ምክንያት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብንና የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ፣ ሀገሪቷን ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚወስዱ ማናቸውንም ድርጊቶችን የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ያነገበ መሆኑ ታውቋል።።
 በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን፣ እንዲሁም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ በተለይም የሀገርን ሉዐላዊነት የሚገዳደሩ፣ የፌደራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በክልሉ እንዳይወጣ ከማድረግ ባሻገር፣ ሀገሪቷን ወደ ጦር አውድማነት የሚያስቀይሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎችን ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈፀመ ይገኛል።
ይህን ሁኔታ በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን የጠቆመው መግለጫ፤ በህገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ እና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን መቆጣጠር በማስፈለጉ አዋጁ መታወጁን ከመግለጫው መረዳት ተችሏል።
አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈፃሚ የሚደረግ ሲሆን፣ እንደያስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ ወይም ቀሪ የሚሆንባቸውን ተጨማሪ አካባቢዎችን ግብረኃይሉ በሚያወጣው መመሪያ ይወስናል ተብሏል።

LEAVE A REPLY