ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ውጥረት የነገሠባት የትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ እስካሁን በህወሓት ልዮ ኃይል ቁጥጥር ሥር ብቻ እንደምትገኝና ሌላ ወታደራዊ ኃይል እንደሌለ ዘገበ።
ከትላንት እኩለ ለሊት ጀምሮ መቀሌ ከተማ ተኩስ ይሰማ እንደነበር የገለጸው በስፍራው የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ በጊዜው የከተማው ሰው እየሆነ ባለው ነገር ተደናግጦ እንደነበርም አስታውሷል።
“ይሄን ሁኔታ ለማረጋገጥ ወደ ፀጥታ ኃይል ሰዎች ስደውል አሁን ልናናግርህ አንችልም፤ ቢዚ ነን አሉኝ፤ ከደቂቃዎች በኋላ የስልክ መስመር ተቋረጠ። ስልኬም ኖ ሰርቪስ የሚል ምልክት ያሳየኝ ጀመር። በመቀጠል የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ” ያለው የቢቢሲ የመቀሌ ዘጋቢ፤ ጠዋት ከተማዋን ጨምሮ የትግራይ ክልል ሙሉ ለሙሉ መብራት እንደጠፋ ማረጋገጥ ችያለሁ ሲል የነበረውን ሂደት ይፋ አድርጓል።
በከተማዋ ላይ ያሉ የባንክ ቅርንጫፎች ተዘግተው የዋሉ ሲሆን፣ አገልግሎት ያቋረጡት የበይነ መረብ ወይም ኢንተርኔትአገልግሎት ስለሌለ ብቻ መሆኑም ታውቋል።
“ከፀጥታ ኃይል ሰዎች እንደተረዳሁት ተኩሱ የተሰማው የትግራይ ክልል ወታደሮች ከሰሜን ዕዝ ጋር በነበራቸው የተኩስ ልውውጥ መሆኑን ተረድቻለሁ። ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮና ወደ ሌሎች የጉዞ ወኪሎች አምርቼ ለጊዜው በረራ ሙሉ በሙሉ መቋረጡን ተመልክቻለሁ” ያለው የቢቢሲ ዘጋቢ፤ መቀሌ ከተማ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ሆቴሎች አካባቢ ከበድ ያለ የፀጥታ ኃይል መኖሩንም አስታውቋል።
የክልሉ መንግሥት ክልሉ ውስጥ ምንም ዓይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር አግዷል በማለት አሁን ያለውን የከተማዋን ገጽታ የጠቆመው ቢቢሲ፤ የትራንስፖርት አገልግሎትም ሙሉ በሙሉ ቆሟል። የክልሉ የአየር ክልልም ከበረራ ውጭ እንዲሆን ታዟል። መቀሌ ከተማም አሁን ላይ ሰላማዊ ሁኔታ ላይ ትገኛለች” ብሏል