ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በምዕራብ ትግራይ ድንበር በኩል አሁንም ግጭቶች መኖራቸውን የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል አስታወቁ።
ከትናንት በስቲያ ሌሊት የጀመረውና አሁንም በቀጠለው የትግራይና የፌደራል መንግሥት ግጭትን አስመልክቶ አወዛጋቢው የህወሓትና የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ለትግራይ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ላይ ነው ይህ አስተያየት የተሰማው።
እየተካሄደ ያለው ውጊያ ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ ቀጥሏል ያሉት ዶ/ ር ደብረፂዮን በየትኛው ግዛትና የትኞቹ ቦታዎች ላይ እንደሆኑ ከመግለፅ ተቆጥበዋል።
የአማራ ልዩ ኃይልና የፌደራል ሠራዊቱ በጥምረት በመሆን ከትግራይ ኃይል ጋር በትናንትናው ዕለት ጥቅምት 25/ 2013 ዓ.ም መዋጋታቸውንም አረጋግጠዋል።
የትግራይ ኃይል በክልሉ የሚገኙትን የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ጦር መሳሪያም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር አውሏል የሚል አስገራሚ አስተያየት የሰጡት የክልሉ ፕሬዝዳንት፤
“ትግራይ በሚገኙ የጦር መሳሪያዎች የትግራይ ሕዝብ ጥቃት ሊፈፀምበት አይገባም፤ አሁን በሙሉ ታጥቀናል። በጦር መሳሪያ ከነሱ ያነስን አይደለንም፤ ምናልባት የተሻልን ነን” ሲሉም ተደምጠዋል።
ድንበር አካባቢ ሰፍረው የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአዲያቦ በኩል አድርገው ወደ ኤርትራ ድንበር ተሻግረዋል በማለት የተናገሩት ደብረፂዮን፤ የሠራዊት አባላቱ ትግራይ ክልል ከሚቆዩ ወደ ኤርትራ እንዲሻገሩም ትዕዛዝ ተሰጥቷቸውም ነው ይህን ያደረጉት ብለዋል።