ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የመከላከያ ሠራዊት ዳንሻን፣ ባከርን እና ከሽራሮ አስከ ሽሬ ያሉ አካባቢዎችን ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠረ የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ምክትል ኤታማዦር ሹም እና የኦፕሬሽን ዘርፍ ሓላፊ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።
ለኢትዮጵያ ነቀርሳ የሆነው ከሀዲው የህውሓት ቡድን ካልተደመሰሰ ሀገር ሰላም እንደማትሆን የተናገሩት የኦፕሬሽን ዘርፍ ሓላፊው፤ የመከላከያ ሠራዊቱ ዳንሻን፣ ባከርን እና ከሽራሮ አስከ ሽሬ ያሉ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ወደ ፊት እየተጓዘ መሆኑን አስታውቀዋል።
መከላከያ በከሀዲ ቡድኑ እጅ ያሉ ከባድ መሳሪያዎች ሙሉ በሙሉ ማውደሙንና እንደ ተምች በየቦታው ሠራዊቱን የከበበውን ኃይል እያራገፈ እንደሚገኝ የጠቆሙት ጀነራል ብርሃኑ ጁላ፤ ትናንሽ ክፍሎችን ከቦ የነበረው ኃይልም በሠራዊታችን ታላቅ ጀግንነት እንደተደመሰሰም ገልጸዋል።
ብዛት ያለው የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ምርኮኛ እየሆነ እንደሚገኝ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሠራዊቱ እያሳየ ያለው ድጋፍ ከፍ ያለ የሞራል ልዕልና እንዳላበሰው ነው የተነገረው።
ለኢትዮጵያ ነቀርሳ የሆነውን ከሀዲ ቡድን በመደምሰስ የሕግ የበላይነትና ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማረጋግጥ በብቃት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ጀነራሉ፤ የመከላከያ ኃይሉ ሕዝብ እንዳይጎዳ ለማድረግ ሕዝብ እና ጽንፈኛ ኃይሉን ለይቶ ለመምታት በጥንቃቄ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።