ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአማራ ክልል ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ ተስመገን ጥሩነህ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ የሓላፊነት መልቀቂያ ደብዳቤ አስገቡ።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለክልሉ ምክር ቤት የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤውን ያስገቡት እየተካሄደ ባለው የአማራ ክልል መደበኛ ጉባዔ ላይ መሆኑን የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
አሁን ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በተሰጣቸው አዲስ ተልዕኮ ምክንያት ጥያቄውን ያቀረቡት ርእሰ መስተዳድሩ፤ ፓርቲያቸው በተሰለፈበት ሀገርን የማዳን ሥራ ላይ የሚጠበቅባቸውን ለማበርከት አዲሱን ሹመት መቀበላቸውን ለምክር ቤት አባላቱ አብራርተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በመልቀቂያ ደብዳቤው ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ የአቶ ጥሩነህን ጥያቄ በመቀል፤ በምትካቸው አቶ አገኘሁ ተሻገርን ለርዕሰ መስተዳድር በእጩነት እንዳቀረቡ ታውቋል።
ዛሬ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገሌግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተሾሙት አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ለረዥም አመታት የሠሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሓላፊነቱ እንደማይከብዳቸው ይጠበቃል።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ሌሎች የክልሉ አመራሮች በተገደሉበት ወቅት የነበረውን የክልሉን የፖለቲካ ጡዘት ባላቸው ሠፊ የደህንነትና የመረጃ ልምድ ሊቆጣጠሩትና ሊያረግቡት ይችላሉ በሚል መሾማቸውን የሚናገሩ የኢትዮጵያ ምንጮች አሁን ሀገሪቱ ላለችበት ሁኔታ ግለሰቡ ወደ ደህንነት ቢሮ መዛወራቸው ተገቢ ነው ብለዋል።