ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና ሱማሊያውያንን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው አፍሪካዊያን ስደተኞች በታንኳ አቆራርጠው ስፔን ካናሪ ደሴት መግባታቸው ተሰማ።
1ሺኅ የሚሆኑት ስደተኞች ወደ ደሴቲቱ የገቡት ቅዳሜ ዕለት መሆኑን የጠቆሙት የስፔን የአስቸኳይ እርዳታ ሰጪዎች፤ ከተለያዮ ሀገራት የመጡት አፍሪካውያን ስደተኞቹ በ20 ጀልባዎች ላይ ተፋፍገውና ተጭነው፣ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በማለፍ በሕይወት መድረስ ችለዋል ብለዋል።
በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኝ የነበረ አንድ ሰው ወዲያውኑ በሄሌኮፍተር ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ከመሆኑ ውጪ ቀሪዎቹ ስደተኞቹ በመልካም ጤንነት ላይ መገኘታቸው ተሰምቷል።
ካለፉት አምስትና ሥድሥት ወራት ወዲህ ካናሪ አይላንድ ለመግባት የሚጣጣሩ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ ተወላጆች በብዛት እየታዮ ነው። ከዚህ ቀደም ብዙ ስደተኞች የጉዞ መስመራቸው ጣሊያን እንደነበር አይዘነጋም።
በያዝነው አመት ብቻ 11 ሺኅ አፍሪካዊያን ወደ ስፔኗ ካናሪ ደሴት የገቡ መሆናቸውን የጠቆሙት የስፔን ባለሥልጣናት፤ባለፈውሚ ዓመት ወደ ደሴቲቱያ መግባት የቻሉት 2 ሺኅ 557 ብቻ እንደነበሩም አስታውሰዋል።
በጀልባ ጉዞ ከሚያደርጉት ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ ለበርካታ ጊዜያት ሬሳቸው ባሕር ላይ የሚቀር ብዙ አፍሪካዊያን መኖራቸውን የሚያስረዳው ዜና፤ ለምሳሌ በዚህ ዓመት ብቻ 414 አፍሪካዊያን በዚህ አቋራጭ መንገድ በጀልባ ስፔን ካናሪ ደሴት ለመግባት ሲሞክሩ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ያሳያል።