ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ለሥራ ጉዳይ ነው በሚል ምክንያት የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ወደ ተለያዩ መኖሪያ ቤቶች እና ተቋማት የሚሄዱ ግለሰቦችን ማንነት መለየት እና ማረጋገጥ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የህወሓት ሕገ ወጥ ቡድን ተላላኪዎች የከተማችንን ሰላም ለማደፍረስ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን ከሕዝብ በተገኘ ጥቆማ እና የፀጥታ አካላት ባደረጉት ክትትል ማረጋገጥ ተችሏል ያለው ኮሚሽኑ በመሆኑም ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሕገ ወጥ ቡድኑ ተላላኪዎችን ተልዕኮ ለማክሸፍ እና በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባከናወነው ተግባር፤ በርካታ የጦር መሣሪያዎችን እና ለጥፋት መፈጸሚያ ሊውሉ የነበሩ የተለያዩ ንብረቶችን ከእነተጠርጣሪዎቹ ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑንም በመግለጫው ላይ ይፋ አድርጓል።
ከተያዙት ንብረቶች መካከል የተለያዩ የፀጥታ አካላት የደንብ አልባሳት በግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተገኙ መሆናቸውን ተከትሎ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የፀጥታ አካላቱን የደንብ ልብስ በመልበስ እና ተመሳስለው በመንቀሳቀስ የህወሓት ሕገ ወጥ ቡድን ተላላኪዎች ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ በመገመት አስፈላጊው የክትትል ሥራ እየሠራ መሆኑንም አስታውቋል።
የከተማችን ነዋሪዎች የፀጥታ አካላትን የደንብ ልብስ በመልበስ ለሥራ ጉዳይ በሚል ምክንያት ወደተለያዩ መኖሪያ ቤቶች እና ተቋማት የሚሄዱ ግለሰቦችን ማንነት በትክክልም የፀጥታ አካል ስለመሆን፣ አለመሆናቸው የተቋማቸውን የሥራ መታወቂያ ጠይቀው መለየት እና ማረጋገጥ እንዳለባቸው ዛሬ የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ ላይ በግልፅ አስቀምጧል።
ፖሊስም ሆነ ሌሎች የፀጥታ አካላት የሥራ መታወቂያ እንዲያሳዩ በተጠየቁ ጊዜ የማሳየት ግዴታ እንደተጣለባቸው ያሳሰበው ኮሚሽኑ፤ መታወቂያቸውን ለማሳየት ፈቃደኛ ያልሆኑ የፖሊስ አባላት ሲያጋጥሙ በመጠራጠር መረጃ እና ጥቆማውን በየአቅራቢያቸው ለሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች በአካልም ሆነ በስልክ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል ብሏል።