አንድ ህብረ ዝማሬ – ቃል-ኪዳን ነበረን፣
በአንድነት ያቆመ – በአንድ ያስተሳሰረን፣
በፅኑ ተጋምዶ እጅግ የደደረ፣
ዘመናት ያለፈ – ዘመናት የኖረ፣ በላብ የከበረ፣
በደምና በአጥንት የተመሰጠረ፣
በእኔና አንተ መሃል – ቃል-ኪዳን ነበረ።
ከአንተ በፊት ያርገኝ
እኔን ያስቀድመኝ
አንተን ክፉ አይንካህ
እንኳን ሌላው ቀርቶ – ዕንቅፋት አይምታህ
የሚል ቃል ነበረን – በእምነት የቀለመ፣
በሀገር ፍቅር ላይ -ፀንቶ የታተመ!
በየተራራው ላይ – “ላብ ደምን ይተካል” እያልን ስንሮጥ፣
ከፍ ባለ ሞራል – ሶምሶማ ስንረግጥ፣
አምባው ሲንቀጠቀጥ – በሕብረ ድምፃችን፣
በአንድ መቆም ነበር – ደግሞም አብሮ መሞት -የሁሌ ቃላችን!
ኮቾሮ በድንጋይ – ቀጥቅጠን አልመን፣
የቆርቆሮውን ወጥ _ በብረት ባርኔጣ – ገንፈልፈል አድርገን፣
ፍርፍር ቢጤ ሰርተን – እየተጎራረስን፣
ከአንድ ኮዳ ውሃ – ተካፍለን ጠጥተን፣
“ተመስገን” እያልን – በፍቅር ያፀናነው – ቃል-ኪዳን ነበረን!
“ፋሉል ብረት” እሣት – ከላይ ሲዘንብብን፤
አንድ ላይ ልንወድቅ – ወድቀን ልንነሳ – ቃል-ኪዳን ነበረን!
የመድፍና የታንክ ነጎድጓድ ወላፈን፣
ከፀሐይ ንዳድ ልቆ ሲያነደን ሲልፈን
አይዞን ተባብለን፤
ለአንደኛችን መኖር – ከአንዳችን ፊት ቀድመን
ሞትን እንደ ፀጋ – በእምነት ተቀብለን፣
ስለ ሀገር ክብር፣
ሕይወት ልንገብር – በአንድ ዓላማ ፀንተን፣
በደም የከተብነው – ቃል-ኪዳን ነበረን።
ቃልኪዳን ነበረን – በደም የፀደቀ – በግብር የደመቀ፣
እንኳንስ ያገሩን – የአፍሪካን ወንበዴ – በፅናት ያረቀ፣
ቃል-ኪዳን ነበረን – የማይነቃነቅ፣
ዓለምን ያስቀና – እያደር የሚደምቅ!
በሠላሙ ጊዜ – በአንድ ጋቤጣ እየጠጣን “ስዋ”
ቃልኪዳን ነበረን – አብረን ልንሰዋ!
“አደይ ማርያም” ብለን – አብረን ተገባብዘን፣
በአንድ ትሪ በልተን – በአንድ ዋንጫ ጠጥተን፣
በሐቅ ያደመቅነው _- ቃልኪዳን ነበረን!
የክፉ ቀን ጓድህ – የክፉ ቀን ጓዴ፣
በእምነት ተቆላልፈው – ክንድህና ክንዴ፣
በፍቅር ተጋምደን – በፅናት የቆምን – አልነበርንም እንዴ!?
ምነው በለሊቱ – በድቅድቅ ጨለማ – በድንገት ከዳኸኝ፣
አንተ አለኸኝ ብዬ -የእግዜር ዕንቅልፍ ወስዶኝ፣
አድብተህ እንደአውሬ – እንደእባብ ነደፍከኝ፣
እንዳይሆን አድርገህ ልቤን ሸቀሸቅከኝ!
“አገር አማን ብዬ – ወገን አለኝ ብዬ – ሳሸልብ ጠብቀህ፣
ማተብህን ጥለህ – እምነቴን በጥሰህ፣
ስታዘንብ ጥይት በሰውነቴ ላይ፣
በስተመጨረሻ – ዐይቼህ ነበረ – በቁም ስትሰቃይ፣
ይብላኝ እንጂ ለአንተ – እኔ እንደታመንኩት
ነፍሴ ከመውጣቷ – ከማለፌ በፊት፣
እንደተለመደው – ቃል እንደገባሁት፣
“ኢትዮጵያ ወይም ሞት!” – ብዬ ነው የሞትኩት!
ሀገር አልከዳሁም – ወገን አልከዳሁም
ቃል አላፈረስኩም!
ስሄድ እንኳ ከዓለም “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ማለት አልረሳሁም!
“ኢትዮጵያ ወይም ሞት!!
ሕዳር 1 ቀን 2013 ተጻፈ።

























