10 ጋዜጠኞች መታሰራቸው በእጅጉ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ

10 ጋዜጠኞች መታሰራቸው በእጅጉ እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ

የአዲስ ስታንዳርድ መፅሄት አዘጋጅ መድሃኔ እቁባሚካኤል እንደገና ለእስር መዳረግ፣ የአውሎ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በቃሉ አላምረው በቁጥጥር ስር መዋል በእጅጉ እንዳሳሰባቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ገለፁ።
ከሚዲያ ጋር የተገናኘ ጥፋት ጠፍቶም ከሆነ ፍትሃዊ በሆነ መንገድና ስርአትን በተከተለ ሁኔታም እንዲካሄድ በትዊተር ገጻቸው ያሳሰቡት ኮሚሽነሩ፤ ሁኔታውንም በቅርበት እንደሚከታተሉም አስታውቀዋል።
ከላይ ከተገለጹት ሁለቱ ጋዜጠኞች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች የሆኑት ሃፍቱ ገብረ እግዚአብሐር፣ ፀጋዬ ሃዱሽና አብርሃ ሃጎስ እንዲሁም፤ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርኩ ጋዜጠኛ ኡዲ ሙሳና አራት ጋዜጠኞች በአንድ ምሽት መታሰር ስጋት እንደፈጠረባቸውም ዶክተር ዳንኤል ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
“በማንኛውም ጊዜ የሰዎችን ከህግ አግባብ ውጪና ኢፍትሐዊ በሆነ መልኩ ያለመታሰር መብት እንዲከበር ጥሪ እናቀርባለን” ሲሉም ጠንካራው የሰብኣዊ መብት ተሟጋች የድርጅታቸውን አቋም ለመንግሥት በግልጽ አስቀምጠዋል።
ሀብቶም ገብረ እግዚአብሔርና ፀጋዬ ሀጎስ በኢዜአ ስር በሚታተመው የእንግሊዝኛው ሄራልድ ጋዜጣ አዘጋጆች ሲሆኑ፤ አብርሃ ሀጎስ ደግሞ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአረብኛው ክፍል አል ዓለም ላይ በሪፖርተርነት የሚሠራ ነው።
በተመሳሳይ በጋዜጠኞች መብት ላይ የሚሠራው ሲፒጄ በበኩሉ የአውሎ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በቃሉ አላምረው እንዲፈታ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጥሪ ማቅረቡ ተሰምቷል።
ጋዜጠኛው ጥቅምት 25/ 2013 ዓ.ም በቁጥጥር ስር እንደዋለና ክስም እንዳልተመሰረተበት የጠቆመው ሲፒጄ፤ ሦስት የፖሊስ መለዮና አንድ የሲቪል ልብስ የለበሱ ግለሰቦች አዲስ አበባ ወደሚገኘው የአውሎ ሚዲያ ማዕከል ቢሮ በማምራት ጋዜጠኛ በቃሉን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

LEAVE A REPLY