አለማችን ብዙ የሚደነቁ የጦር መሪዎች ነበሯት። የእንግሊዙ ዊንስተን ቸርችልና የሮማው ጁሊዬስ ሴዛር በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱት መካከል ይገኙበታል ። ችርችል ለንደን በሂትለር ጄቶች ስትደበደብ ተስፋ ባለመቁረጥ ህዝቡን ከሁዋላው አሰልፎ ለድል የበቃ ጀግና ነው። ለቸርችል ከናዚ ጋር ድርድር ብሎ ነገር በፍጹም የሚታሰብ አልነበረም። የቸርችል ታንኮች ጸጥ ያሉት የናዚ ታንኮች ከሰገዱ በሁዋላ ነው።
የጥንቱን የሮማ መሪ ጁሊዬስ ሴዛርን ደግሞ ማግነስ ፖምፒዮ የተባለው አጋሩ ከዳው። መክዳት ብቻ አይደለም በአድማ ከስልጣን አወረደው። ጁሊዬስም ወደ ፈረንሳይ ተሰደደ። በስደት ላይ ሆኖም ጦር አደራጀ። የጁሊየስ ጦር ገና የሮምን ድንበር ሲረግጥ፣ ፖምፒዮ ስልጣኑን ለቆ ወደ ስፔን ሸሸ። አማካሪዎቹም ” በቃ ፖምፒዮም ሸሽቷል፤ አንተም በፍጥነት ወደ ሮም ሂድና ከተማዋን አረጋጋት ” አሉት። ጁሊዬስ ግን ” በፍጹም” አለ። ” ፖምፒዮን እስከመጨረሻው ካላጠፋሁት ተመልሶ እንደሚያጠፋኝ አውቃለሁ” አለና ጥቂት ታማኞቹን ይዞ ወደ ስፔን አቀና። ስፔን ላይ በነበረው ውጊያ ፖምፒዮ ተሸነፈ። ነገር ግን እጅ ሳይሰጥ ባህር አቋርጦ ወደ ግብጽ ሸሸ። አማካሪዎቹም በድጋሜ ” እባክህ ሮም እየተሰቃየች ነው። እንመለስና እናረጋጋት።” አሉት። ጁሊዬስ ግን “ተውኝ” አለ። ግብጽ ሲደርስ ፖምፒዮ በክሊዮፓትራ ወንድም እጅ መገደሉን ሰማ። ልብ በሉ ጁሊዬስ ባላንጣውን ፍለጋ ሲንከራተት ሮም ለ 10 ዓመታት ያክል መንግስት አልነበራትም ።
እነዚህ ሁለት ጀግኖች ከድል በሁዋላ በአለም ላይ እስከዛሬ የሚታወሱባቸውን ታላላቅ ስራዎች ሰርተው አልፈዋል። ችርችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአውሮፓ ህብረት የመሳሰሉ ተቋሞች እንዲመሰረቱ ደክሟል። (በነገራችን ላይ ታንክ የሚባለው የጦር መሳሪያም የእሱ ሃሳብ ነው። ታንክ ሲፈጠር የውሃ ታንከር ነበር የሚባለው። ይህ ስያሜ የተሰጠበት የራሱ አስገራሚ ታሪክ አለው። ሌላ ጊዜ አነሳው ይሆናል።) ጁሌዬስ ሴዛርም የጁሊያን ካላንደርን ጨምሮ ዛሬ ስራ ላይ እየዋሉ ያሉ ብዙ የህግ ሃሳቦችን አመንጭቷል። በእንግሊዝኛ ጁላይ (July) የሚባለው ወርም ይህን ጀግና ለማስታወስ የተሰጠ ስያሜ ነው።
አብይ አህመድ አብሪ የሆነ ታሪክ መጻፍ ከፈለገ የእነዚህን ሁለት መሪዎች ፈለግ መከተል አለበት ብዬ አምናለሁ። ህወሃት ሙሉ በሙሉ ሳይጠፋ ኢትዮጵያን መልሶ መስፋትም ሆነ ማስፋት አይቻልም። ማስፋት ስል ፖለቲካውን እንጅ መሬት እያልኩ አይደለም። በመንግስት ላይ የሚደርሰውን የዲፕሎማሲ ጫና እረዳለሁ። የጦርነት ባህሪ ሆኖ ማጥቃት ከመከላከል በላይ ዋጋ እንደሚያስከፍልም አውቃለሁ። ነገር ግን ምንም አይነት ጫና ይኑር፣ መከፈል ያለበት መስዋትነት ተከፍሎ፣ ህወሃት ሙሉ በሙሉ ካልተደመሰሰ ኢትዮጵያ እንደ አገር ለመቀጠል ትቸገራለች ። ግማሽ ድል ማለት ሙሉ ድል ማለት አይደለም። አንድ የጀርመን ጄኔራል እንዳለው ” ትርፍ የሌለው ስምምነት በጦርነት እንደመሸነፍ የሚቆጠር ነው። ለህወሃት ዳግም እስትንፋስ መስጠት ማለት መርዛማ እባብ ይዞ ሰርከስ ላይ መደነስ ማለት ነው። እጅ ስለመስጠት መደራደር ይቻላል፤ በጋራ እጅ ስለመስጠት ( white-peace) መደራደር ግን የሚታሰብ ነገር መሆን የለበትም። White-peace ማለት አሸናፊም “አሸንፌያለሁ”፣ ተሸናፊም “ተሸንፌያለሁ” ሳይል የሚደረግ ስምምነት ነው።