ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢትዮጵያ ሠራዊት ከትግራይ ዋና ከተማ መቀለ በስተሰሜን የምትገኘው የአዲግራት ከተማን ዛሬ ቅዳሜ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩ ተረጋገጠ።
አዲግራት ከተማ የምሥራቃዊ ትግራይ ዞን ማዕከል ስትሆን ከመቀለ 116 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የምትገኘው የአዲግራት ከተማን መያዙ በትግራይ ዋና ርዕሰ መዲና የሚገኘውን ወታደራዊ ጁንታ ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ እንደሚያስችለው እየተነገረ ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ ጽ/ቤት ዛሬ ኅዳር 12 ቀን 2013 ዓ.ም ሠራዊቱ አዲግራት ከተማን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠሩን ሲያረጋግጥ፤ የትግራይ ክልል መገናኛ ብዙኃን ድርጅት በፌስቡክ ገጹ “ትናንት ምሽት በአዲግራት ከተማ ላይ የከባድ መሳሪያ ድብደባ መፈጸሙንና በዚህም ሠላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል” የሚል ክስ ከመግለጹ ውጪ፤ ከተማዋ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ስለመዋሏ ምንም ሳይል አልፎታል።