ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በትግራይ ክልል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በ167 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱን ገለፀ።
በህወሓት ኃይሎች የተፈጸሙት ተግባራት በሀገሪቱ የወንጀል ሕግ አንጻር በከፍተኛ ወንጀል የሚያስጠይቁ መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፤ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት የመንግሥትን ሀገሪቱን የመከላከል ኃይል ለማዳከም በተፈጸመ ወንጀል በሚል የሚያስጠይቅ መሆኑንም አስረድተዋል።
በባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ላይ የተፈጸሙት የሮኬት ጥቃቶች ድርጊቱ በሽብር ወንጀል እንደሚያስጠይቅ የገለጹት ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፤ በተጨማሪም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ፣ ታጥቆ አመጽ መቀስቀስ እና በሀገር ክህደት ወንጀሎች የሚያስጠይቁ ወንጀሎች ፈጽመዋል ብለዋል።
“ሕግ የማስከበር ዘመቻው የተራዘመው ለንፁሃን ዜጎች ቅድሚያ በመስጠታችን ነው” ያሉት ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ፤ እስካሁን ድረስ በፌደራል ፖሊስ እና በፌደራል ዐቃቤ ሕግ የተለዩ 167 ተጠርጣሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው፣ ከእነዚህም መካከል በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።