ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ በሰላምና ደህንነት መስኮች እንዲሁም ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ።
የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ የሞሳድ ቢሮ ኃላፊ ጋር በዛሬው ዕለት ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመከላከል እና ከሥሩ በመንቀል ረገድ ያላት አቋም ጠንካራ መሆኑን የጠቀሱት የእስራኤል የሞሳድ ዳይሬክተር ጀነራል ሚስተር ዮሴፍ ኮ`ን ልዩ መልዕክተኛ እንዲሁም በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ የሞሳድ ቢሮ ኃላፊ የህዝቦች የጋራ ጠላት የሆነውን ሽብርተኝነትን በተቀናጀ ሁኔታ ለመከላከል ሞሳድ ከኢትዮጵያ አቻ የመረጃና ደህንነት ተቋም ጋር በትብብር እንደሚሰራና ድጋፋኑም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያና እስራኤል በባህል፣ በሃይማኖት፣ በታሪክና በፖለቲካው ዘርፎች የረጅም ጊዜ ግንኙነት የመሰረቱ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመረጃና ደህንነት ዘርፉ ያላቸውን ተቋማዊ ግንኙነት እያጠናከሩ መምጣታቸውን ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል።