ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የወጭ አሥተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጠራው ይፋዊ የሕዝብ ውይይት፣ ተጠሪው መሥሪያ ቤት የሚጠበቅበትን ሥራ ከውኖ ባለመገኘቱ ውይይቱ ሳይካሄድ ለመበተን ተገደደ።
የፕላንና ልማት ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦች የሚያስፈልጉ መዋቅሮችን አዋቅሮ ፋይናንስ የሚፈልግ ኮሚቴ አለማዋቀሩ ፣ በግሉ ዘርፍና በሲቪክ ማህበራት በኩል ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር በተያያዘ የሚከወኑ ሥራዎችን መረጃ አለመሰብረቡ፣ የመረጃ ቋትም እንዳልሰበሰበ የተደረገው የኦዲት ሪፖርት አጋልጦ ነበር።
የተጠቀሱት የኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ ሥራ መከወኑን ለማረጋገጥ ቋሚ ኮሚቴው ለዛሬ ሰኞ ህዳር 28 ቀን ጥሪ ደርሶት በስብሰባው ላይ ቢገኝም፣ “ፕላን ኮሚሽን ከኦዲት ግኝቱ ግልፅ ያልሆኑልኝ ነገሮች አሉ፤ ከዋና ኦዲተር ጋር በጉዳዩ ላይ ተነጋግረን ለሌላ ጊዜ ማብራሪያ ብሰጥ መልካም ነው”በማለት በኮሚሽነሯ ፍፁም አሰፋ በኩል ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ውይይቱ ሳይካሄድ ተበትኗል።