የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ አለኝታ… || አቶ ዳኛቸው ይልማ አረፉ!

የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ አለኝታ… || አቶ ዳኛቸው ይልማ አረፉ!

የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ከተመሰረተበት 1983 ዓ.ም ጀምሮ፤ የኮምፒዩተር ህትመት ስራዎችን በማስተዋወቅ፤ ነጻው ፕሬስ በዘመነ መልኩ እንዲሰራ ካደረጉት፤ ቀደምት የፕሬሱ አባላት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት፤ አቶ ዳኛቸው ይልማ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ስንገልጽ፤ ለቤተሰባቸው፣ ለወዳጆቻቸውና እንዲሁም ለስራ አጋሮቻቸው መጽናናትን በመመኘት ነው።

አቶ ዳኛቸው ይልማ… በኢትዮጵያ ይታተሙ ከነበሩት ጋዜጦች መካከል፤ በአቶ ክፍሌ ሙላት ዋና አዘጋጅነት ለህትመት የሚበቃውን “ዜና አድማስ” ጋዜጣ በአሳታሚነት ሰርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ወቅት ይታተሙ ከነበሩ በርካታ ሳምንታዊ ጋዜጦች መካከል ከአስር በላይ የሚሆኑትን ጋዜጦች በቅድመ-ህትመት ስራ ያግዙ የነበሩ አንጋፋ የፕሬሱ አጋር ነበሩ።

አቶ ዳኛቸው ይልማ… ከፕሬሱ በተጨማሪ “ፒያሳ ኮምፒዩተር ማዕከል” እና በስበኋላ ደግሞ፤ የማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ መስራች በመሆን፤ እንደዶ/ር አብይ አህመድ እና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ለማፍራት የበቁ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን መኩሪያ ነበሩ። አቶ ዳኛቸው ይልማ በኢህአዴግ ስርአተ መንግስት እንደብዙ ኢትዮጵያዊያን ከአቅም በላይ በሆነ ፖለቲካዊ ጫና ምክንያት ከአገር ቤት ወጥተው ላለፉት ስምንት አመታት ኑሯቸውን በአሜሪካ ማድረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ አሁን በአገር ቤት በተፈጠረው ለውጥ ምክንያት፤ ከዚህ በፊት ይሰሩበት የነበረውን የማይክሮ ሊንክ ኮሌጅ ከባልደረቦቻቸው ጋር ለማደራጀት ወደ አገር ቤት ተመልሰው ስራ ጀምረው ነበር። ሆኖም ሙሉ ለሙሉ አገር ቤት ገብተው ስራ ከጀመሩ ከጥቂት ወራት በኋላ ዲሴምበር 6 ቀን፣ 2020 በድንገተኛ ህመም ሆስፒታል ቢገቡም፤ ለመዳን ሳይችሉ ቀርተዋል።

አቶ ዳኛቸው ይልማ ባለ ትዳር እና የሁለት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ።

በውጭ አገር የምንገኝ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች በአቶ ዳኛቸው ይልማ ህልፈተ ሞት የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን፤ እየገለጽን፤ ለመላው ቤተሰቡና ወዳጆቹ መጽናናት ይሆን ዘንድ፤ ለአቶ ዳኛቸው ይልማ የZoom መታሰቢያ ዝግጅት በመጪው እሁድ ጠዋት፤ ከ10፡00 AM EST ጀምሮ የሚከናወን መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እናሳውቃለን።

በውጭ አገር የምንገኙ የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች ፎረም

ሰብሳቢ – ዳዊት ከበደ ወየሳ

ለተጨማሪ 703 582 6079 – 713 572 5484 – 678 437 5597 – 650 387 4940 – 47 47154 122

LEAVE A REPLY