ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ሲባል ወደ ጃንሜዳ እንዲዘዋወር የተደረገው የአትክልት ተራ ከነበረበት ሥፍራ የማንሳት አገልግሎቱ ተጀምሯል።
ብዙ ውዝግብ ያስነሳው ባሕረ ጥምቀቱ የሚገኝበትና ታላላቅ ስፖርታዊ ውድድሮች (በተለይም አትሌቲክስ) የሚካሄድበት ጃን ሜዳ የአትክልት ተራ ነጋዴዎች በተዛወሩበት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደቆሻሻ ማጠራቀሚያነትና በመጥፎ ጠረን የተበከለ አካባቢ ለመሆን እንደበቃ ይታወሳል።
የጥምቀት በዓል መድረሱን ተከትሎ ጃንሜዳን ማፅዳት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተጀምሮ የነበረው ከ10 ቀን በፊት በምንሊክ፣ ሽሮሜዳና የፈረንሳይ ለጋሲዮን ወጣቶች የነበረ ቢሆንም፤ በወቅቱ ከመንግሥት ከበላይ አካል ታዘን ነው የመጣነው ያሉ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት “ማን ፈቅዶላችሁ ነው የምታፀዱት?” በሚል ወጣቶቹን ከአካባቢው እንዲባረሩ አድርገዋል።
ዛሬ ም / ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ባልደረቦች በመታጀብ ጃንሜዳን የማፅዳት ዘመቻ እንደተጀመረ ያበሰሩበትንና ለሚዲያ ፕሮፐጋንዳ ፍጆታ የሚውል የአምስት ደቂቃ የማፅዳት ተግባር ከውነው ወደመጡበት ተመልሰዋል።
በጃን ሜዳ የተከማቸው ቆሻሻ ከመጠን በላይ በመሆኑና አሁንም ስፍራውን እንዲለቁ የታዘዙ በርካታ ነጋዴዎች በመደቦቻቸው ላይ ተቀምጠው ሥራቸውን እያካሄዱ በመሆናቸው ጃን ሜዳ በትክክል ለጥምቀት በዓል ፀድቶ ማለቁ አጠራጣሪ ሆኗል።