ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በእስክንድር ነጋ የሚመራው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ህወሓት እና ኦነግ ሸኔ በአሸባሪነት እንዲፈረጁ ዛሬ በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ ጠይቋል።
ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑ ድርጅቶች ፖለቲካን ሽፋን አድርገው በዘረፉት ገንዘብ የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች ተወርሰው ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም ሊውሉ ይገባል ያለው ባልደራስ፤
አሁን ያለው ሕገ መንግሥት የህወሓትና የኦነግ የበኩር ልጅ በመሆኑ ባስቸኳይ ከምርጫ በፊት ታግዶ ሕዝቡ ተወያይቶ አዲስ የመተዳደሪያ ሊመሠረት ይገባል ብሏል።
በህወሓት በኅይል የተነጠቁ ከሰሜን ጎንደር ( ወልቃይት ጠገዴ ጠለምትና ሁመራ ) እንዲሁም ከሰሜን ወሎ በኅይል የተነጠቀው ራያ ወደ ቀድሞ ይዞታው አማራ ክልል እንዲካተት መደረጉ አግባብና ፍትሃዊ መሆኑን እንደሚያምን ያስታወቀው ፓርቲው፤ የህሊና(የፖለቲካ) እስረኞችን ጨምሮ የባልደራስ ከፍተኛ አመራሮች እነ እስክንድር ነጋ የኢዴፓ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ልደቱ አያሌው ባስቸኳይ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።