ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 93ኛው መደበኛ ስብሰባ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ የካፒታል ገበያ ባደገበት ሀገር አምራች ኩባንያዎች የአክስዮንና የብድር ሰነዶችን በመሸጥ የረዥም ጊዜ እና የአደጋ ሥጋት ያለባቸውን፣ ነገር ግን የምርታማነት ባህሪ ያላቸውን ፕሮጀክቶች በቀላሉ ፋይናንስ ማድረግ የሚያስችል የአዋጅ ማሻሻያ መደረጉ ተገልጿል።
በሁለተኛ ደረጃ የካፒታል ገበያ ለህብረተሰቡ አማራጭ የቁጠባ መንገዶችን በማቅረብ የኢኮኖሚውን የፋይናንስ ቁጠባ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆመው መግለጫ፤
ይህ ኢንቨስትመንት በሀገር ውስጥ ቁጠባ ፋይናንስ እንዲሆን በማድረግ ከውጭ ፋይናንስ ያለንን ጥገኝነት ይቀንሰዋል ሲል አስረድቷል።
እነዚህንና ሌሎች የካፒታል ገበያ ጥቅሞችን ታሳቢ በማድረግ ረቂቅ አዋጁ በብሄራዊ ባንክ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ በዝርዝር ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲመራ መወሰኑ ታውቋል።