በአውስትራሊያ የትህነግ ቤ/ክናት ሰማያዊና ዓለማዊ መግለጫ … || ሳምሶን አስፋው

በአውስትራሊያ የትህነግ ቤ/ክናት ሰማያዊና ዓለማዊ መግለጫ … || ሳምሶን አስፋው

በአውስትራሊያ የሚገኙ 5 የትህነግ ቤ/ክርስቲያናት ያወጡትን የጋራ መግለጫ አነበብኩት። ለስለስ ብሎ በመንፈሳዊ ድባብ የሚጀምረው መግለጫ ቀስ በቀስ እየጠነከረ ይወርድና በመጨረሻም እንደ ጁንታው አመራሮች በማስፈራራት ይቋጫል። ካህን ጀምሮት ካድሬ የቋጨው የሚመስል በተቃርኖ የተሞላ ሰማያዊና ዓለማዊ መግለጫ ነው።

ታላቁን መጽሃፍ ገልጦ (የሐዋርያት ሥራ 20: 28) በመጥቀስ መንፈሳዊ መልዕክቱን የሚጀምረው መግለጫ፤ አያይዞም “እንሆ እናንተ ግን መንጋውን ትጠብቁ ዘንድ የተሰጣችሁን ሃላፊነት አልተወጣችሁም” በማለት የሲኖዶሱን ጳጳሳት ይወቅሳል። የትግራይ ህዝብ ሲጨፈጨፍ ዝምታን መረጣችሁ በሚል ውንጀላ ዛሬም በትግራይ ሕዝብ ሊነግድ ይሞክራል። እውነታው ግን የሲኖዶሱ ጥበቃ የተነፈገው መንጋ አረመኔው የጁንታው ሠራዊት እንጂ የትግራይ ህዝብ አለመሆኑ ነው።

በመንፈሳዊ ዲስኩር እያዋዛ የጀመረው መግለጫ ወዲያው ደግሞ ፖለቲካዊ መልዕክቱን ያስከትላል። የምድራዊውን መተዳደሪያ ጥራዝ “ህገ-መንግስቱን” ይገልጥና “ብልጽግና ፓርቲ ህጋዊ ስልጣን የለውም! “ ሲል ይሞግታል። በአንድ ግዜ ሁለት ክስ ይመሰርታል። ሲኖዶሱን በሰማያዊው ችሎት ብልጽግናን በዓለማዊው ችሎት ይከሳል። ግን በሁለቱም ይረታል…!

በነገራችን ላይ ትህነግ የ5ቱም ቤተ ክርስቲያናት ባለቤት መሆኑን የሚያውቀው በአውስትራሊያ የሚገኝው ኢትዮጵያዊ በጋራ መግለጫው ያልተለመደ ፖለቲካዊ ይዘትም ሆነ ጭልጥ ያለ ወገናዊነት አይገረምም።

መግለጫው ሃተታውን ሲቋጭ ፤ ሲኖዶሱ የተለያዩ 4 እርምጃዎች እንዲወስድ ያሳስብና ፤ በመቀጠልም “ይህን ካላደረጋችሁ አማራጭ እርምጃ ልንወስድ እንገደዳለን” በማለት ያስፈራራል።

ለመሆኑ አማራጭ እርምጃው ምን ይሆን ? የሚለውን ጥያቄን ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። አማራጭ እርምጃው በቅርቡ ከዋናው ሲኖዶስ የሚገነጠል (ይቅርታ የሚሰነጠር) የጁንታው መታሰቢያ ሲኖዶስ ያረገዘ ይሆን…?

ያገርሽ ይሆን ወይ የሲኖዶስ ጣጣ
የውጪው ሲገባ የውስጡ እየወጣ … ?

የሚለውን ጥያቄ እንመርምር ? እውን የመግለጫው ማስፈራሪያ ሚዛን ያነሳል? ምንስ ድረሰ ሊጓዝ ይችላል?፡

በኔ እይታ ማስፈራሪያው ሚዛን የሚያነሳ አይደለም። የጁንታውን አቅም ያገናዘበም አይደለም። ለምን/እንዴት ማለት ጥሩ!

“አማራጭ እርምጃ እንወስዳለን” የሚለው ማስፈራሪያ፤ ለ25 ዓመታት ተለያይቶ ቆይቶ ከ 3 አመት በፊት በዶ/ር አቢይ ሸምጋይነት አንድ የሆነውን ሲኖዶስ ዳግም ለሁለት እንከፍለዋለን! ወይም እንገነጠላለን የሚል ቀጲጸ ተስፋ የያዘ ይመስላል። ይሁንና በውጭው አለም ያለውን የጁንታውን የድጋፍ መጠን ጁንታውን አምርሮ ከሚጠላው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ጋር ስናመዛዝነው ማስፈራሪያው ከንቱ፤ የከንቱ ከንቱ ሆኖ እናገኘዋለን። የጁንታው ድጋፍ እንኳን ከመላው ኢትዮጵያዊ ቀርቶ በቅርቡ ነጻ ከወጣው በትግራይ ከሚገኘው የትግራይ ህዝብ ቁጥር ጋም የሚመጣጠን አይደለም..…

በመጨረሻም የምሰናበታችሁ፤

ለ27 አመት … በሰፈሩት ቁና፤
ዛሬ ሲሰፈሩ … ዙር ተራ ሆነና፤
ላማ ሰበቅታኒ – ኤሎሄ አሉ እሪ…
ቁናውን ሲያዘጋጅ አዲሱ ሰፋሪ ።

የሚሉትን ስንኞች በመጋበዝ ነው

ቸር ይግጠመን

LEAVE A REPLY