ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በእስክንድር ነጋና ሌሎች የባልደራስ ከፍቸኛ አመራሮች የፍርድ ቤት ቀጠሮ ላይ የነገሥታቱን ምስል እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያለበትን ቲሸርት ለበሳችኋል በሚል የታሰሩ የባልደራስ አባላት ዛሬ ፍ/ቤት ቀረቡ።
እነዚህ ወጣቶች ዛሬ አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት መቅረባቸውን ለኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢ የገለጹት የባልደራስ የህግ ጉዳዮች ሓላፊ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ፤ ፖሊስ ያቀረበው የክስ ጭብጥም እጅግ አሳዛኝም አስቂኝም ነበር ብለዋል
በወጣቶቹ ላይ አድዋ የጥቁር ህዝቦች ኩራት ነው፣ ታሪክ የማያስተምራቸው ታሪክን ይደግማሉ የሚሉ ጽሑፎች የሰፈሩባቸው ቲሸርቶችና የዳግማዊ አፄ ምንሊክ እና የንግስት ጣይቱን ምስል ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ጋር ያለበት ቲሸርት ለብሰው ፤ በአዲስ አበባ ኹከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲሞክሩ ያዝኳቸው ሲል ፖሊስ ክስ መስርቷል ነው ያሉት የህግ ባለሙያው።
ዛሬ ወጣቶቹ ፍርድ ቤት ሲቀርቢ ፖሊስ የምርመራ ሥራዬን ስላላጠናቀኩ ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠን ሲል ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው ቲሸርቱን መልበስ በወንጀል የማያስጠይቅና ሆን ተብሎ አባላቱን ለማሸማቀቅ፣ እንዲሁም በታሪክ እንዲያፍሩ የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የማያሰጥ ነው በማለት ተክራክሯል።
የሁለቱን ወገኖች ክርክሩን ያደመጠው ፍ/ቤት ፖሊስ ምርመራውን እስከ ነገ ጠዋት ጨርሶ እንዲቀርብ አዝዞ፤ ተከሳሽ የሆኑት የባልደራስ አባላትም እስር ቤት እንዲቆዮ መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል።