እነ እስክንድር ነጋ “ፍትህ…ፍትህ” በማለት በችሎት ቢጮሁም ዳኞች ለመጋቢት ቀጠሮ ሰጡ

እነ እስክንድር ነጋ “ፍትህ…ፍትህ” በማለት በችሎት ቢጮሁም ዳኞች ለመጋቢት ቀጠሮ ሰጡ

 ኢትዮጵያ ነገ ዜና– እነ እስክንድር ነጋ ዛሬም በችሎት ፍትህ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ቀጥተኛ የመንግሥት ትእዛዝ ይዘው የመጡት ዳኞች ከአራት ወር በኋላ የሚታይ የችሎት ቀጠሮ ሰጡ።
ዛሬ ችሎቱ የተሰየመው ዐቃቤ ህግ ያሻሻለውን ክስ በማየት የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለማድመጥ የነበረ ቢሆንም ችሎት የተሰየሙት ዳኞች ገና ሲገቡ ከፊታቸው ላይ መልዕክት አድራሽነታቸው በግልጽ ይታይ እንደነበር ታዝበናል።
ወንጀሉን ፈፅመሀል ወይስ አልፈፀምክም? የሚል ጥያቄ የቀረለት እስክንድር ነጋ አለመፈጸሙን ገልጾ “ከሁሉም በፊት ሁሉን በሚያየውና ሁሉን በሚሰማው እግዚአብሔር ስምእዚህ ተከሰን ችሎት ፊት የቆምነው አራታችንም ንፁህ መሆናችንን እገልፃለሁ። ጥፋተኛ ብቻ አይደለንም ሳይሆን ይህ ክስ አንድም ዕውነት የለበትም። ሁሉንም በማታዩት በፍ/ቤቱ በህዝብና በታሪክ ፊት ግን እውነት ዘግይቶም ይሁን ፈጥኖ እንደሚወጣና ነፃ እንደሚያደርገን አምናለሁ።”
ሲል ቃሉን ሰጥቷል።
ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዮም እና አስካለ ደምሴም በተመሳሳይ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ገልጸው የቀረበባቸው ክስ ሙሉ ለሙሉ ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረድተዋል።
የባልደራስ አመራር እስክንድር ነጋ ጉዳያቸው በህግ እየታየ በዋስ እንዲወጡ ችሎቱን ከመጠየቁ ባሻገር “ሕዝብ በቀጣዮ ምርጫ ስለሚጠብቀን መሳተፍ ይኖርብናል” ሲል ጠይቋል።
ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለመጋቢት 29 ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተበትኗል። ረዥሙን ቀጠሮ ተከትሎ እነ እስክንድር “ፍትህ ፍትህ ፍትህ” እያሉ ደጋግመው ቢጮሁም እነርሱንም ሆነ ሕዝቡን ማየት የፈሩ የሚመስሉት ዳኞቹ የመጡበትን ፈጽመው፣ እንዳቀረቀሩ ሹልክ ብለው ወጥተው ሄደዋል።

LEAVE A REPLY